ብልፅግና ፓርቲ ያለተፎካካሪ የተወዳደረባቸውን በርካታ ወንበሮች ማሸነፉ ሲገለጽ፣ ተቃዋሚዎችም ብልፅግና ያልተወዳደረባቸውን ወንበሮች ማሸነፋቸውን ቀጥለዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ከፊል ውጤት ማሳወቁን በመቀጠል፣ ዛሬ ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጠው 3ኛ ዙር መግለጫ የሌሎች 32 የምርጫ ክልሎችን ውጤት አፅድቆ ይፋ አድርጓል።

የቦርዱ የስነ-ዜጋ ትምህርት ኃላፊ አርማዬ አሰፋ ባነበቡት በዚህ ውጤት መሠረት፣ በታወጁት መቀመጫዎች ላይ የገዢው ብልፅግና ፓርቲ አብዛኛዎቹን ወንበሮች መጠቅለሉን ቢቀጥልም፣ ሁለት የፓርላማ መቀመጫ ማሸነፋቸው ከታወጀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መሪ አቶ ኢዮብ መሳፍንትን እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካሸነፉት የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ዕጩ አቶ መኮንን ጎለሳ በተጨማሪ፣ በድሬዳዋ ከተማ ምክር ቤት ሦስት የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ወንበሮችን አግኝተዋል። ዛሬም፣ የምክር ቤቶች ወንበሮችን የማሸነፍ ድል የቀናቸው አምስት ተቃዋሚዎች ብልፅግና ፓርቲ በተወዳዳሪነት ባልቀረበባቸው መቀመጫዎች መሆኑ ታውቋል።

በተቃራኒው፣ ዛሬ ብልፅግና ፓርቲ እንዳሸነፋቸው ከተገለጹት ወንበሮች መካከል አራቱ የፓርላማ እና 14ቱን የክልሎች ምክር ቤቶች ወንበሮች ተቃዋሚዎች ምንም ዕጩ ያላቀረቡባቸው ነበሩ።
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በጥቅሉ የ11 የምርጫ ክልሎች ውጤት ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ዘጠኙን ወንበሮች ብልፅግና ፓርቲ አሸንፏል። ገዢው ፓርቲ ያሸነፋቸው የምርጫ ክልሎች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሊሞ 02፣ በአማራ ክልል ራቤል (ብልፅግና ብቻውን የተወዳደረበት)፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ሰባት የምርጫ ክልሎች (አለም ጤና፣ በሌ፣ ያዮ፣ ዲምቱ፣ ጎባ፣ ግንደ በረት እና ኩርፋ ጨሌ) ናቸው።

በተለይ በያዮ ምርጫ ክልል የኦሮሚያ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ ብቻቸውን በዕጩነት የቀረቡ ሲሆን፣ ዛሬ መመረጣቸውን ምርጫ ቦርድ ካፀደቀላቸው ተወካዮች ወገን ተሰልፈዋል።

በአንጻሩ ቀሪው ዛሬ ውጤቱ የታወጀው አንድ የፓርላማ ወንበር በአዲስ አበባ ከተማ፣ የምርጫ ክልል 18 ላይ ከኢዜማ ፓርቲ የተወዳደሩት የፓርቲው መሪ አቶ እዮብ መሳፍንት ማሸነፋቸው ተገልጿል። በዚህ የምርጫ ክልል ብልፅግና ዕጩ ያላቀረበ ሲሆን፣ ከኢዜማ ውጭ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሕዳሴ ፓርቲ፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት እና የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወዳድረው ነበር።

በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካማሺ ምርጫ ክልል፣ ብልፅግና ተፎካካሪ ዕጩ ያላቀረበበትን አንድ የፓርላማ ወንበር የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ዕጩ አቶ መኮንን ጎለሳ አሸንፈዋል። 

ለክልል ምክር ቤቶች በጠቅላላው የ21 የምርጫ ክልሎች (በድምሩ የ66 መቀመጫዎች) ውጤት ይፋ ሆኗል። ከእነዚህ ውስጥ ድሬዳዋ 15 የምርጫ ክልሎች (45 ወንበሮች)፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ 1 የምርጫ ክልል (6 ወንበሮች)፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 1 የምርጫ ክልል (3 ወንበሮች) እና ኦሮሚያ 4 የምርጫ ክልሎች (12 ወንበሮች) ይገኙበታል። ከእነዚህ 66 መቀመጫዎች ውስጥ 63ቱን ብልፅግና ሲያሸንፍ፣ 3ቱን የድሬዳዋ ከተማ ምክር ቤት ወንበሮች የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪሎች አሸንፈዋል።

በክልል ምክር ቤቶች ውጤት መሠረት ተቃዋሚዎች በ3ኛ ደረጃነት ያሸነፏቸው ሦስት መቀመጫዎች በሙሉ በድሬዳዋ የምርጫ ክልሎች ስር የሚገኙ ሲሆኑ፣ እነሱም በጀሎ ምርጫ ክልል አቶ ረመዳን መሀመድ ሰኢድ (አዲስ ትውልድ ፓርቲ)፣ በኩርቱ ምርጫ ክልል አቶ ጀማል ኡመር ኢብራሂም (ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ) እና በቢዩ አዋሌ ምርጫ ክልል አቶ አብዱላሂ ፋራህ መሀመድ (ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ) ናቸው።

ለእነዚህ ሦስት ወንበሮች ብልፅግና ዕጩ አላቀረበም ነበር። ቀሪዎቹን የድሬዳዋ 12 የምርጫ ክልሎች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጭሪ ልዩ ምርጫ ክልል (3 ወንበሮች)፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካማሺ (6 ወንበሮች) እና የኦሮሚያ አራት የምርጫ ክልሎችን (ያዩ፣ ሀብሮ 2፣ ገላን አባያ እና ጎባ፣ 12 ወንበሮች) ሙሉ ለሙሉ ብልፅግና አሸንፏል።

ዛሬ በታወጁት የምርጫ ውጤቶች 5ቱን የፓርላማ እና 14 የክልሎች ምክር ቤቶች የምርጫ ክልሎች ውስጥ ብልፅግና ያሸነፈው፣ የትኞቹም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጩ ባላቀረበቡት ነው።

ምርጫ ቦርድ ሰኔ 2 እና ሰኔ 3 ቀን የ46 የምርጫ ክልሎችን ውጤት አፅድቆ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው። ዛሬ ሰኔ 4 ቀን የተገለጹትን ውጤቶች ጨምሮ፣ እስካሁን በጥቅሉ የ33 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ወንበሮች እና የ151 የክልል ምክር ቤት ወንበሮች (በድምሩ 184 መቀመጫዎች) ይፋዊ ውጤት ታውቋል።

እስካሁን ይፋ በተደረገው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፊል ውጤት መሠረት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ከተሰጡት 33 መቀመጫዎች ውስጥ 30ዎቹን የገዢው ብልፅግና ፓርቲ ሲያሸንፍ፣ ቀሪዎቹን 3 ወንበሮች ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች የሆኑት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ዕጩዎች ማሸነፍ ችለዋል።

ለክልል ምክር ቤት ከተላለፉት ወንበሮች መካከል 5ቱን መቀመጫዎች የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች ያሸነፉ ሲሆን፣ እነሱም የቤኒሻንጉል ሕዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ 1 ወንበር፣ የኦጋዴን ነፃነት ግንባር 1 ወንበር፣ እንዲሁም በድሬዳዋ አዲስ ትውልድ ፓርቲ 1 ወንበር እና ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ 2 ወንበሮችን በማግኘት ድል አስመዝግበዋል።

በሌላ በኩል፣ የቦርዱ የመረጃ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ሺመልስ ሲሳይ እንደገለጹት፤ እስካሁን 1,131 ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶች ተጠቃለው ወደ ማዕከሉ የገቡ ሲሆን፣ 8 የምርጫ ክልል ውጤቶች (7 በሶማሌ ክልል እና 1 በአማራ ክልል) አሁንም ድረስ ወደ ማዕከል አልደረሱም። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ501 መቀመጫዎች ውስጥ 497ቱ የደረሱ ሲሆን 4ቱ አልቀረቡም፤ ከክልል ምክር ቤት ደግሞ ከ638 መቀመጫዎች ውስጥ 634ቱ ሲደርሱ 4ቱ አልደረሱም።

ቦርዱ በውጤት ማረጋገጫ ቡድኑ ስር ያዋቀራቸው 94 የኦዲት ባለሙያዎች የምስክር ወረቀቶችን መሠረት በማድረግ እስከ ምርጫ ጣቢያ ድረስ የማመሳከር ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት እልባት ሊገኝላቸው ባለመቻሉ ወደ 250 የሚሆኑ ውጤቶች ወደ ኦዲት የተላኩ ሲሆን፣ እነዚህ ውጤቶች ተመርምረው ድጋሚ ምርጫ ይደረጋል የሚል ውሳኔ ሊተላለፍባቸው እንደሚችል ተገልጿል። የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በሰጡት መግለጫ ደግሞ፣ ቦርዱ ከቀረቡት 120 የሚሆኑ ቅሬታዎች መካከል 148 ምስክሮችን ተቀብሎ እያስተናገደ መሆኑን ጠቅሰው፣ ምስክሮች በሰዓቱ አለመገኘት ለሂደቱ ተግዳሮት እንደሆነባቸውና ማጣሪያ ተደርጎ ውሳኔ ያልተሰጣቸው የምርጫ ክልል ውጤቶች ይፋ እንደማይደረጉ አስታውቀዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)