የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ በጉራጌ ዞን እና በምሥራቅ ጉራጌ ዞኖች ስር በሚገነኑ ስምንት የምርጫ ክልሎች ላይ የምርጫውን ውጤት ፍጹም ሊያስቀይር የሚችል መሠረታዊ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን አስታወቀ።
ፓርቲው ትናንት ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ በምርጫው ሂደት በወንጀል ሊጠየቁ የሚገባቸው አካላት እንዳሉ ጠቁሟል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የፓርቲው ይፋዊ አቤቱታ እንደደረሰው ገልጾ፣ ቅሬታ ከተመዘገበባቸው 120 የምርጫ ክልሎች መካከል የጎጎት ጥቆማዎች እንደሚገኙበት አረጋግጧል።
የጎጎት ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ መሐመድ አብራር በመግለጫው ላይ ገዢውን ፓርቲ በጥብቅ የኮነኑ ሲሆን፣ “ገዢው ፓርቲ ራሱ ተወዳዳሪ፣ ራሱ አስፈጻሚ፣ በአብዛኛው በሕዝቡ ስም ራሱ ድምፅ ሰጪ እና ራሱ ድምፅ ቆጣሪ ሆኖ ሂደቱንና ውጤቱን ራሱ በፈለገው መንገድ ብቻ የመራበት ምርጫ ተደርጓል” ሲሉ ወቅሰዋል።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ነዋሪዎችን “ጎጎትን ከመረጣችሁ መንግሥት ይበቀላችኋል” በሚል ማስፈራሪያ ሲሰጥ እንደነበር የጠቀሰው ፓርቲው፤ በዕለተ ምርጫው የማጭበርበር እና ኮሮጆ የመገልበጥ ሥራ በግልጽ ሲሠራ ተቃውሞ ላቀረቡ ታዛቢዎች የሚሰጠው መልስ “ከላይ የመጣ አቅጣጫ ነው” የሚል እንደነበር አጋልጧል። በዚህም ምክንያት ምርጫው የሕዝብ ሉዓላዊ ውሳኔ መሆኑ ቀርቶ የበላይ አካል ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሆኗል ብሏል።
ፓርቲው በዋናነት የተፈጸሙ ጥሰቶች ያላቸውን ዝርዝር ሲያቀርብ፣ የተደራጁ ሰዎችን ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ አንድ ሰው ተደጋጋሚ ድምፅ እንዲሰጥ ማድረግ፣ መራጮች ወደ ጣቢያ ሲመጡ መታወቂያ አለመጠየቅ እና የሐሰተኛ ድምፅ መስጫ ወረቀቶችን በብዛት ጥቅም ላይ ማዋል፣ መራጮች የድምፅ መስጫ ወረቀት ሲሰጣቸው ማንን እንደሚመርጡ በአስገዳጅ ሁኔታ መጠየቅ፣ እንዲሁም ድምፅ አሰጣጥ ከመጀመሩ በፊት የፓርቲውን ወኪሎች ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ መከልከል እና በቆጠራ ወቅት ወኪሎችን አስፈራርቶ ከጣቢያ ማስወጣት ናቸው ብሏል።
ፓርቲው በእነዚህ ከባድ ጥሰቶች ምክንያት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በክልል ምክር ቤት ውድድሮች ላይ መሠረታዊ የውጤት ለውጥ ያመጣሉ ያላቸውን አቤቱታዎች በጥቅሉ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በይፋ አስገብቷል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከግል ዕጩዎች በጥቅሉ የ120 የምርጫ ክልሎች አቤቱታ የደረሰው መሆኑን ገልጸው፣ የጎጎት ፓርቲ ያቀረባቸው ስምንት የምርጫ ክልል አቤቱታዎችም ከእነዚህ ቅሬታ ከቀረበባቸው ማዕከላት መካከል እንደሚገኙበት በይፋ አረጋግጠዋል።
“ለመሆኑ ከሁለቱ የጉራጌ ዞኖች ውጪ ያለውን የምርጫ ውጤት ትቀበላላችሁ ወይ?” ስትል “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለሰነዘረችላቸው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት አቶ መሐመድ አብራር፣ ቅሬታ ካቀረቡባቸው ከእነዚህ ስምንት የምርጫ ክልሎች ውጪ ያሉት የአካባቢዎች ውሎ በአንጻራዊነት የተሻለ የሚባል እንጂ ችግር ያለበት ነው የሚያስብል እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በመሆኑም በምርጫ ክልል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በክልል ደረጃም የሚቀበሏቸው ውጤቶች እንዳሉ ጠቁመው፣ ጉዳዮቹን በሕጉ መሠረት በመለያየት እንደየሁኔታው የሚቀበሉ መሆኑን አስታውቀዋል።
የፓርቲው ፕሬዚዳንት አክለውም “ፓርቲው የምርጫውን ውጤት ለመቀበል በዋነኝነት ቦርዱ በገለልተኝነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን በማጣራት በሚያወጣው መግለጫ ላይ የተመሠረተ ነው” ብለዋል። ቦርዱ ቅሬታዎቹን መርምሮ ሲያጠናቅቅ ፓርቲው እንደ አስፈላጊነቱ የተጠቃለለ ይፋዊ መግለጫ እንደሚሰጥም ታውቋል።
ጎጎት ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በአጠቃላይ 82 ዕጩዎችን ያቀረበ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 21ዱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ቀሪዎቹ ደግሞ ለክልል ምክር ቤት የቀረቡ ናቸው። ዕጩዎቹ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ፣ ሲዳማ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ እንደሚወዳደሩ ይታወቃል።
ፓርቲው ትናንት በሰጠው መግለጫ ላይ ለ12 መገናኛ ብዙኃን ጥሪ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ በቦታው የተገኙት 3 የሚዲያ ተቋማት ብቻ መሆናቸው እንዳሳዘነውም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ገልጿል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




