በ25 ድምፅ ወደ ምክር ቤት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የድምፅ ቁጥር የተመረጡ ተፎካካሪ ዕጩዎች መኖራቸው ተገለጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሰኔ 2 እስከ ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣቸው ተከታታይ መግለጫዎች ያፀደቃቸው ከፊል ውጤቶች፣ በርካታ ተፎካካሪ በሌለባቸው የምርጫ ክልሎች የሚወዳደሩ ዕጩዎች እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የመራጮች ድምፅ ወደ ምክር ቤቶች መግባታቸውን አሳዩ።

ቦርዱ እስካሁን ባወጃቸው ውጤቶች ውስጥ ስምንት የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪሎች መመረጣቸው የጸደቀ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ አምስቱ ደግሞ ለክልል ምክር ቤቶች የተመረጡ ናቸው። ይሁን እንጂ ከተመረጡት ስምንት ተቃዋሚዎች መካከል ስድስቱ ከ50 በመቶ በታች የመራጮች ድምፅ ያገኙ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ወደ ምክር ቤት የገቡት ባለ ባለሁለት እና ሦስት አሐዝ የድምፅ ቁጥር ነው።

በእነዚህ ተከታታይ የውጤት እወጃዎች ውስጥ እጅግ ዝቅተኛ በሚባል ድምፅ የተመዘገበው ለድሬዳዋ ከተማ ምክር ቤት በወጣው ውጤት ላይ ነው።

በኩርቱ የምርጫ ክልል ለከተማው ምክር ቤት የተመረጡት የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ዕጩ አቶ ጀማል ኡመር ኢብራሂም ያገኙት አጠቃላይ ድምፅ 25 ብቻ እንደሆነ ተገልጿል። በምርጫ ክልሉ ለመምረጥ የተመዘገቡት መራጮች ቁጥር 2,204 ቢሆንም፣ አቶ ጀማል ያገኙት ድምፅ ከተመዘገቡት መራጮች አንጻር ሲሰላ 1% (አንድ በመቶ) ገደማ ብቻ ነው።

በዚሁ የምርጫ ክልል የተወዳደሩት ሁለቱ የብልፅግና ፓርቲ ወኪሎች ግን የተመዘገቡት መራጮች በሙሉ መርጠዋቸው እያንዳንዳቸው 2,204 እኩል ድምፅ ማግኘታቸውን ቦርዱ አስታውቋል።

ለድሬዳዋ ከተማ ምክር ቤት አንድ የምርጫ ክልል 3 ወንበሮች ያሉት በመሆኑ እና በኩርቱ የምርጫ ክልል ከሦስቱ ዕጩዎች በስተቀር ሌላ የተመዘገበ ተወዳዳሪ ባለመኖሩ አቶ ጀማል በዚሁ ዝቅተኛ ድምፅ ወደ ምክር ቤት መግባታቸው ተረጋግጧል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በድሬዳዋ ከተማ የጀሎ በጂና የምርጫ ክልል ተመራጭ መሆናቸው የጸደቀላቸው የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ተወካይ አቶ ረመዳን መሐመድ ሰኢድ፣ 6,001 መራጮች በተመዘገቡበት የምርጫ ክልል ውስጥ 200 ድምፅ ብቻ በማግኘት ወደ ምክር ቤት ሊገቡ መሆኑ ታውቋል።

አቶ ረመዳን ያገኙት ድምፅ ከተመዘገቡት መራጮች አንጻር 3 በመቶ ገደማ ብቻ ሲሆን፣ በዚህም የምርጫ ክልል ከሦስቱ ዕጩዎች በስተቀር ሌላ የተወዳደረ አካል አልነበረም። በዚሁ የምርጫ ክልል የተመረጡት ሁለቱ የብልፅግና ወኪሎች እያንዳንዳቸው እኩል 5,993 ድምፅ አግኝተዋል ተብሏል።

በአንጻሩ ቢዮ አዋሌ በሚባለው የድሬዳዋ የምርጫ ክልል የተወዳደሩት ሌላው የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ዕጩ አቶ አብዱላሂ ፋራህ መሐመድ፣ ከተመዘገቡት 4,537 መራጮች መካከል 1,675 (37 በመቶ) ድምፅ ማግኘት ችለዋል። በዚህም የምርጫ ክልል ከሦስቱ ዕጩዎች ውጭ ሌላ 1 ያላሸነፈ የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ የነበረ ሲሆን፣ ሁለቱ አሸናፊ የብልፅግና ዕጩዎች 4,469 እና 3,870 ድምፅ አግኝተዋል።

እስካሁን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ለክልል ምክር ቤትም ሆነ ለፓርላማ ለመግባት የሚያስችል እውነተኛ የአብላጫ ድምፅ ያገኙትና ከ50 በመቶ በላይ የመራጮችን ድምፅ ማግኘት የቻሉት ሁለት ዕጩዎች ብቻ ናቸው።

የመጀመሪያው በሶማሌ ክልል ደጋህቡር የምርጫ ክልል ለሶማሌ ክልል ምክር ቤት መመረጣቸው የጸደቀላቸው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ተወካይ አቶ መሀሙድ ሀሰን ሁሴን ሲሆኑ፣ የተመዘገቡ መራጮችን 73% ድምፅ (ከ86,828 መራጮች ውስጥ 62,971 ድምፅ) በማግኘት አሸንፈዋል።

ሁለተኛው ደግሞ በአማራ ክልል ጎንደር ዙሪያ 4 የምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) የተመረጡት አቶ ጣሂር መሀመድ ጣሂር ሲሆኑ፣ ከ44,925 የተመዘገቡ መራጮች መካከል የ26,604 (59 በመቶ ገደማ) መራጮችን ድምፅ አግኝተዋል።

ከእነዚህ ከሁለቱ ተመራጮች ውጭ ያሉት ቀሪዎቹ ስድስት የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪሎች ግን በሙሉ ከ50 በመቶ በታች ድምፅ ማግኘታቸውን የቦርዱ የውጤት እወጃ ያሳያል።

በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 18 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመረጡት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) መሪ አቶ እዮብ መሳፍንት 42% ድምፅ፣ እንዲሁም የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ዕጩ ሆነው የቀረቡት አቶ መኮንን ጎለሳ በ43% ድምፅ ተመራጭነታቸው ጸድቆላቸዋል።

እስካሁን ለክልልም ሆነ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመረጣቸው የጸደቀላቸው ስምንቱም የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪሎች ያሸነፏቸው ወንበሮች በሙሉ፣ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ በተወዳዳሪነት ዕጩ ያላቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች መሆናቸው ታውቋል። የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቀደም ሲል ለፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ፣ ፓርቲያቸው የተቃዋሚዎችን ውክልና በምክር ቤቶች ለማሳደግ ሲል “ሆነ ብሎ እንደሚሠራ” መናገራቸው ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም ፓርቲው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በርካታ የፓርላማ እና የክልል ምክር ቤት ወንበሮች ላይ ዕጩ ሳያቀርብ መቅረቱ የሚታወስ ነው። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)