በዚህ ሳምንቱ የመንግሥታት ምሥረታ ሰባት ክልሎች ነባር ርዕሰ መስተዳድሮቻቸውን ሥልጣን ሲያራዝሙ፣ አራቱ ክልሎች አዳዲስ አመራሮችን ሰይመዋል

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መሠረት፣ ካለፈው ሰኞ መስከረም 18 ቀን 2019 ጀምሮ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም 11 የክልል ምክር ቤቶች የመንግሥት ምሥረታ ጉባዔዎቻቸውን አካሂደዋል።

በመሥራች ጉባዔዎቹ ሰባት ክልሎች ማለትም ሐረሪ፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ እና አፋር ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ በድጋሚ ተመርጠዋል።

በተቃራኒው ከቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በመውጣት እንደ አዲስ የተዋቀሩት ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች፣ እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አዳዲስ መሪዎች የተሾሙባቸውን ጉባዔዎች አካሂደዋል።

የመንግሥት ምሥረታ ጉባዔውን በቀዳሚነት ሰኞ መስከረም 18 ቀን 2019 ያካሄደው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ክልሉን ሲመሩ የቆዩትን አቶ ሽመልስ አብዲሳን በድጋሚ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር አድርጎ ሾሟል። በዚሁ ጉባዔ ላለፉት አምስት ዓመታት ክልሉን በምክትል ርዕሰ-መስተዳደርነት የመሩትን አቶ አወሉ አብዲን በመተካት አቶ ከፍያለው ተፈራ የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ሆነው ተሹመዋል።

ከሁለት ቀናት በኋላ ረቡዕ መስከረም 20 ቀን 2019 የመንግሥት ምሥረታ ጉባዔውን ካካሄዱት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በከንቲባነት እንዲቀጥሉ በድጋሚ መርጧል። ሆኖም በጉባዔው ከተማዋን በምክትል ከንቲባነት ሲመሩ የነበሩትን አቶ ዣንጥራር አባይን በመተካት፣ ደሴ ከተማን በተቀዳሚ ከንቲባነት የመሩት አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ተሹመዋል። አቶ ሳሙኤል ከዚህ ኃላፊነታቸው በተጨማሪ የከተማዋን ፕላንና ልማት ቢሮ እንዲመሩ ተመድበዋል።

በዚያኑ ቀን የመሥራች ጉባዔውን ያካሄደው የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድን በርዕሰ-መስተዳደርነት፣ እንዲሁም ዶ/ር ጋትሉዋክ ሮንን በምክትል ርዕሰ-መስተዳደርነት እንዲቀጥሉ አድርጓል። ሁለቱ አመራሮች ክልሉን እንዲመሩ በቅድሚያ የተሾሙት ነሐሴ 2016 በተጠራ አስቸኳይ ጉባዔ ነበር።

ሐሙስ መስከረም 21 ቀን ደግሞ የሶማሌ፣ የአማራ እና የሲዳማ ክልል ምክር ቤቶች የመንግሥት ምሥረታ ጉባዔዎቻቸውን አካሂደዋል። ከረፋድ ጀምሮ ጉባዔውን ያካሄደው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አዳዲስ ሹመኞችን ወደ ሥልጣን ያመጣ ሳይሆን፣ አቶ ሙስጠፋ ሙሐመድ እና ምክትላቸው አቶ ኢብራሂም ኡስማን በድጋሚ በርዕሰ-መስተዳደርነት እና በምክትል ርዕሰ-መስተዳደርነት የተመረጡበት ነበር። በተመሳሳይ ቀን የአማራ ክልል ምክር ቤት በመሥራች ጉባዔው ክልሉን ሲያስተዳድሩ የቆዩትን አቶ አረጋ ከበደን እንደገና የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር አድርጎ የሾመ ሲሆን፣ ዶ/ር አብዱ ሁሴን በምክትል ርዕሰ-መስተዳደርነት እንዲቀጥሉ ተደርጓል።

የሲዳማ ክልል በተመሳሳይ ቀን ባካሄደው የመንግሥት ምሥረታ ጉባዔ በተለየ መልኩ በከፍተኛ አመራሩ ላይ ለውጥ የታየበት ነበር። ከክልሉ ምሥረታ ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ደስታ ሌንዳሞ በዶ/ር መሳይ ኃይሉ ተተክተዋል። ዶ/ር መሳይ እስከዚህ ሹመታቸው ድረስ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ ቆይተዋል። የክልሉ ምክር ቤት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ክልሉን በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ በአቶ በየነ ባራሳ ምትክ ዶ/ር ዳዊት ሃይሶን የሾመ ሲሆን፣ ዶ/ር ዳዊት ከዚህ ጎን ለጎን የክልሉን የገንዘብ ቢሮ በኃላፊነት እንዲመሩ ተመድበዋል።

ትላንት ዓርብ መስከረም 22 ቀን 2019 የሐረሪ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የአፋር ክልሎች እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የምሥረታ ጉባዔዎች የሹም-ሽር ውሳኔዎቻቸውን ይፋ አድርገዋል። የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አቶ ኦርዲን በድሪን እንደገና በርዕሰ-መስተዳደርነት፣ ወ/ሮ ሮዛ ኡመርን ደግሞ በምክትል ርዕሰ-መስተዳደርነት መርጧል። አቶ ኦርዲን ክልሉን ላለፉት ስምንት ዓመታት የመሩ ሲሆን፣ ወ/ሮ ሮዛ ደግሞ የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊነትንም ደርበው ይሠራሉ።

ላለፉት አምስት ዓመታት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሆነው የቆዩት ዶ/ር ተስፋዬ በልጅጌ፣ በምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን እንዲመሩ በምክር ቤቱ ተመርጠዋል። ዶ/ር ተስፋዬ ወደ ቦታው የመጡት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውስጥ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙትን የቀድሞውን ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ጥላሁን ከበደን ተክተው ነው። የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት ዶ/ር ደምስ አድማሱ ደግሞ በምክትል ርዕሰ-መስተዳደርነት የተሾሙ ሲሆን፣ የሥራና ክህሎት ቢሮንም በተጨማሪነት ይመራሉ።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በበኩሉ ከንቲባ የነበሩትን አቶ ከድር ጁሀርን ወደ ምክትል ከንቲባነት ያወረደ ሲሆን፣ አቶ አብዱላሂ አደን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ሆነው ተሹመዋል። አቶ አብዱላሂ እስከ ተሾሙበት ጊዜ ድረስ የሶማሌ ክልል ንግድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የመንግሥት ተጠሪ የነበሩትን አቶ ፍቅሬ አማንን በርዕሰ-መስተዳደርነት የመረጠበትን የመንግሥት ምሥረታ ጉባዔ አካሂዷል። ክልሉ ራሱን ችሎ ከተደራጀበት ጊዜ ጀምሮ ክልሉን በርዕሰ-መስተዳደርነት ሲመሩ የነበሩት ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ነበሩ። በሌላ በኩል ምክር ቤቱ አቶ ማስረሻ በላቸው በክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደርነት እና በግብርና ቢሮ ኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ አድርጓል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ2011 ጀምሮ በርዕሰ-መስተዳደርነት የቆዩት አቶ አሻድሊ ሐሰን በዚያው ኃላፊነት እንዲቀጥሉ የክልሉ ምክር ቤት በመሥራች ጉባዔው ወስኗል። እንደ እርሳቸው ሁሉ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ እና ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ተደርጓል።

ትላንት ማምሻውን የአፋር ክልል ምክር ቤት ሐጂ አወል አርባ ክልሉን በርዕሰ-መስተዳደርነት እንዲያስተዳድሩ በድጋሚ መርጧቸዋል። አቶ ሐሚድ ዱላ ደግሞ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር እና የመሬት ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዶ/ር የትምጌታ አስራት ርዕሰ-መስተዳደር ሆነው የተሰየሙ ሲሆን፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት ክልሉን ሲመሩ የቆዩትን ዶ/ር እንዳሻው ጣሰውን ተክተዋል። ዶ/ር የትምጌታ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደርነታቸው እንዲቀጥል የተደረጉት ደግሞ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ናቸው።

በመንግሥታት መሥራች ጉባዔዎቹ በድምሩ የ415 ተሿሚዎች ሹመት የጸደቀ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 282ቱ የካቢኔ አባላት (ሥራ አስፈጻሚዎች) ናቸው።

በሁለቱም እርከኖች የወንዶች የጎላ የበላይነት የታየ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ተሿሚዎች ውስጥ 82.9 በመቶዎቹ ወንዶች ሲሆኑ፣ ለሴቶች የተሰጠው ድርሻ 17.1 በመቶ ብቻ ነው። በካቢኔ አባላት ሹመትም የወንዶች የበላይነት ተስተውሏል፤ 81.2 በመቶ የሚሆኑት ተሿሚዎች ወንዶች ሲሆኑ ሴቶች በካቢኔ አባልነት ያላቸው ድርሻ 18.8 በመቶ ብቻ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በካቢኔ አባላት ስብጥር ከፍተኛውን የሴቶች ቁጥር የያዘ ነው። በካቢኔው ከተካተቱት 23 አባላት መካከል 11ዱ ሴቶች ናቸው። ዝቅተኛው የሴቶች ውክልና የተመዘገበው ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሲሆን፣ ከ13 የካቢኔ አባላት ውስጥ አንዲት ሴት ብቻ በካቢኔው ተካታለች።

የአማራ ክልል በድምሩ 57 አጠቃላይ ተሿሚዎችን በማጽደቅ ከአገሪቱ ከፍተኛውን የተሿሚ ቁጥር የያዘ ሲሆን፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ደግሞ በአጠቃላይ 14 ተሿሚዎችን ብቻ በማጽደቅ አነስተኛውን ቁጥር አስመዝግቧል።

ክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የመንግሥት ምሥረታ በዚህ ሳምንት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በመጪው ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2019 የፌዴራል መንግሥት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መሠረት አዲስ መንግሥት ያቋቁማል ተብሎ ይጠበቃል። ምርጫ ያልተካሄደበትን የትግራይ ክልል ጨምሮ፣ በአማራ ክልል በግጭቶች ሳቢያ ምርጫ ሳይካሄድባቸው የቀሩ ስምንት የምርጫ ክልሎች እንዲሁም በድጋሚ ምርጫ ወይም በድጋሚ ቆጠራ ውጤታቸው ይታወቃል የተባሉ ክፍት የሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች መቼ እንደሚሞሉ እስካሁን በይፋ አልተገለጸም። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)