ዛሬ የተቋቋመው የአዲስ አበባ መስተዳድር ካቢኔ ምን ይመስላል?

ዛሬ ረቡዕ መስከረም 20 ቀን 2019 የመንግሥት ምሥረታ ጉባኤውን ያካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት፣ ለከተማይቱ ምክር ቤት ተወዳድረው ካሸነፉ ተመራጮች ባሻገር የክልል ምክር ቤት አባላትን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችን እንዲሁም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያልተሳተፉ ግለሰቦችን ያካተተ 26 አባላት ያሉት አዲስ ካቢኔ አዋቀረ።

ከረፋዱ ጀምሮ በተካሄደው በዚሁ የምሥረታ ጉባኤ፣ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ፣ ምክትል አፈ-ጉባዔ እና የከተማዋ ከንቲባ በድጋሜ ተመርጠዋል። ባለፈው ግንቦት 24፣ 2018 በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ በከተማ አስተዳደሩ ካሉት 158 ወንበሮች መካከል ገዢው ብልፅግና ፓርቲ 134ቱን ሲያሸንፍ፣ ተቃዋሚዎችና የግል ተወዳዳሪዎች ቀሪዎቹን 24 መቀመጫዎች መጋራታቸው ይታወሳል።

በምክር ቤቱ ከፍተኛ ወንበር ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ ያቀረባቸውን እጩዎች መሠረት በማድረግ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ወ/ሮ ቡዜና አልከድር እና ምክትል አፈ-ጉባዔዋ ወ/ሮ ፈይዛ መሐመድ በነበሩበት ኃላፊነት እንዲቀጥሉ በሙሉ ድምፅ ጸድቋል። በተመሳሳይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማይቱን ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለመምራት በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ-መሐላ ፈጽመዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሹመታቸውን ተከትሎ ያቀረቧቸውና በምክር ቤቱ የጸደቁት 26 የካቢኔ አባላት ሰፋ ያለ ስብጥር ታይቶበታል።

ከንቲባዋ ከካቢኔ አባላቱ መካከል 14ቱ አዳዲስ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በጸደቀው ሹመት 16 ወንዶች እና 10 ሴቶች ተካተዋል። ከአባላቱ መካከል 13ቱ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ተወዳድረው ያሸነፉ (12 የብልፅግና እና 1 የአብን ተወካይ) ሲሆኑ፤ 4ቱ ለደቡብ ኢትዮጵያ፣ አማራ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤቶች ተመራጭ ናቸው። ቀሪዎቹ 9 የካቢኔ አባላት ደግሞ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያልተወዳደሩ ናቸው።

የኃላፊነት ደረጃቸውን በተመለከተ ካቢኔው 1 ምክትል ከንቲባ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ 4 የቢሮ ኃላፊዎች፣ 19 የቢሮ ኃላፊዎች፣ 1 ኮሚሽነር እና 1 ዋና ሥራ አስኪያጅ ይዟል።

ለክልል ምክር ቤት ተወዳድረው አሸንፈው ሳለ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ከፍተኛ ኃላፊነት ከተሰጣቸው መካከል፣ ለሦስት ዓመታት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን በፕሬዝዳንትነት የመሩት አቶ ጥላሁን ከበደ ይገኙበታል። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ የምርጫ ክልል ለክልሉ ምክር ቤት አሸናፊ የሆኑት አቶ ጥላሁን፣ በአዲስ አበባ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነዋል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል ደሴ ከተማ ተወዳድረው ያሸነፉት የቀድሞው የደሴ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ምክትል ከንቲባ እና የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሲሆኑ፤ እንዲሁም በአማራ ክልል በኢፌሶን ምርጫ ክልል ተወዳድረው ያሸነፉት ዶ/ር አህመዲን መሐመድ (በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና መሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ ሁነው ሲያገለግሉ የነበሩ) ደግሞ የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነዋል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሌሞ 01 የምርጫ ክልል አሸናፊ የሆኑት ዶ/ር ተፈራ ሞላ የከተማይቱን ትራንስፖርት ቢሮ እንዲመሩ ተሹመዋል።

በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትም የተካተቱ ሲሆን፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለከተማው ምክር ቤት ያሸነፉት ወ/ት ጽዮን ደረጀ የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ሆነዋል። በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያልተወዳደሩትና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ከነበሩበት የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ወደ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ተዛውረዋል።

በምርጫው ያልተወዳደሩት ሌሎች ሰባት የካቢኔ አባላት አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ፣ አቶ ሙሉቀን ታሪክ፣ አቶ አወሌ መሐመድ ኡመር፣ ኢንጂነር ሔለን ታምሩ፣ አቶ ተስፋዬ ደጀኔ፣ አቶ አስግደው ወልደጊዮርጊስ እና አቶ መላኩ ታምሩ ናቸው። በነበሩበት ኃላፊነት ከቀጠሉት መካከል ደግሞ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊው አቶ ቢኒያም ምክሩ፣ የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ፣ የጤና ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ እና የንግድ ቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ይገኙበታል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)