የአካባቢ ምርጫ ከአንድ ዓመት በኋላ ሊካሄድ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ኀሙስ ኅዳር 17 ቀን 2019 ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ በተካሄደው 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።
በዛሬው የፓርላማ ውሎ የአካባቢ ምርጫን በተመለከተ ምላሽ እና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ተመራጭ ዶክተር አወቀ አምዛዬ ናቸው። የምክር ቤት አባሉ በጥያቄያቸው በኢትዮጵያ የአካባቢ ምርጫ ከተደረገ 15 ዓመታት እየተቆጠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
“የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት የብሔረሰብ ዞን፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ፣ የክፍለ ከተማ ወይም የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ መደረግ እንዳለበት ይደነግጋል፤ ይሁን እንጂ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 14 ዓመታት የአካባቢ ምርጫ አልተደረገም” ያሉት ዶክተር አወቀ፣ በዚህም የተነሳ ከ2005 ጀምሮ ሕዝብ ያልመረጣቸው እና በሕዝብ የማይታወቁ ምክር ቤቶች ‘የሽግግር ምክር ቤቶች’ እየተባሉ ሥልጣን ላይ መቀጠላቸው ትክክል አለመሆኑን አንስተዋል። እነዚህ ምክር ቤቶች “የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ እየሆኑ ነው” ሲሉም ወቅሰዋል።
አክለውም የአካባቢ ምርጫ በፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የጋራ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ንግግር እና የመንግሥት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ውስጥ አለመካተቱ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል። “እስከ ሦስት ዘመን ድረስ ባልተካሄደበት ሁኔታ ‘ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየገነባን ነው’ ማለት ትርጉም አልባ ስለሚያደርገው፣ የአካባቢ ምርጫ የሚካሄድበት የጊዜ ሰሌዳ በፕሬዝዳንቱ ንግግር ውስጥ እንዲካተት፣ ሕዝቡም እንዲያውቀው እና ዝግጅት ይደረግ” በማለት ጠይቀዋል።
ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “በዚህ ዓመት የማሟያ ምርጫን ነው የምናደርገው፤ ከአንድ ዓመት በኋላ የአካባቢ ምርጫ ሊካሄድ ይችላል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “የአካባቢ ምርጫ መደረግ ያለበት ዋናው ምርጫ ከተደረገ በኋላ መካከል ላይ ነው። ዋናውን ምርጫ ደግሞ ያካሄድነው በቅርበት ነው። የዚህ ዓመት ተግባራችን ማሟያ ምርጫ ነው፤ በትግራይ እና በአንዳንድ አካባቢዎች ማሳካት ነው። እሱን ከጨረስን በኋላ ምናልባት ከአንድ ዓመት በኋላ ወደዚያ እንገባለን። ያኔ በፕሬዝዳንቱ ንግግር ይካተታል፤ በዚህ ዓመት ስለማናደርግ ነው እርሳቸው በንግግራቸው ያላስገቡት” በማለት አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አጠቃላይ ምርጫ፣ የአካባቢ ምርጫ፣ ሕዝበ ውሳኔ እና ማሟያ ምርጫን የማካሄድ ሕጋዊ ሥልጣን የተሰጠው ተቋም ሲሆን፣ ቦርዱ ሐምሌ 14 ቀን 2017 በሰጠው መግለጫ ከ2018 አገራዊ ምርጫ በኋላ የአካባቢ ምርጫ እንደሚካሄድ እና ለዚህም ቢያንስ ሦስት ሚሊዮን ዕጩዎች እንደሚያስፈልጉ አስታውቆ ነበር።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአካባቢ ምርጫ የተካሄደው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመመሥረቱ በፊት በ1984 ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድ እስካሁን አራት የአካባቢ ምርጫዎችን አካሂዷል። እነዚህም ሁለተኛው የአካባቢ ምርጫ በ1988፣ ሦስተኛው በ1993፣ ከ1997ቱ አገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ከመደበኛ ጊዜው (1998) ተራዝሞ የተካሄደው አራተኛው የአካባቢ ምርጫ በ2000፣ እንዲሁም አምስተኛው እና ለመጨረሻ ጊዜ የተደረገው የአካባቢ ምርጫ በ2005 የተከናወኑ ናቸው።
ሚያዝያ 6 እና 13 ቀን 2005 በሁለት ዙር በተካሄደው የመጨረሻው የአካባቢ ምርጫ 31.6 ሚሊዮን መራጮች ተመዝግበው ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ድምፅ ሰጥተው ነበር። በወቅቱ ለውድድር ከቀረቡት 3.6 ሚሊዮን የሚጠጉ ዕጩዎች መካከል ከ3.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የቀድሞው ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ እና የአጋር ፓርቲዎቹ ዕጩዎች እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




