የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ ሁለት ቀናት ብቻ እንደቀሩት ዛሬ ሚያዚያ 12፣ 2018 ቀን በማህበራዊ ሚዲያው አሳውቋል።
የመራጮች ምዝገባ ከተጀመረበት ከየካቲት 28፣ 2018 ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 9፣ 2018 ድረስ በጠቅላላው 46,732,895 መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 25,217,202 ወንዶች ሲሆኑ የተቀሩት 21,515,693ቱ ሴቶች ናቸው። ይህ አሃዝ ለ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ከተመዘገቡ አጠቃላይ የመራጮች ቁጥር (40,525,964) ሲነጻጸር የ6,206,931 ብልጫ አለው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሚያዚያ 9፣ 2018 ድረስ አምስት ጊዜ የመራጮችን አሃዛዊ መረጃዎችን ያሳወቀ ሲሆን፤ የመራጮች ቁጥር ከቀን ወደቀን እየቀነሰ መምጣቱን መረጃው ያሳያል።
የካቲት 28፣ 2018 የተጀመረው የመራጮች ምዝገባ ወቅት ለአንድ ወር እንደሚቆይ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ተይዞለት የነበረው አንድ ወር ሲያልቅ ሁለት ሳምንት ተጨምሮ እስከ ሚያዚያ 14፣ 2018 እንደተራዘመ መገለጹ ይታወሳል። [ ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




