የዘንድሮው 7ተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ የካቲት 28፣ 2018 ጀምሮ ትላንት ሚያዝያ 14 ተጠናቋል። በዚህ ከተለመደው በማኑዋል (የእጅ ጽሑፍ እና መዝገብ) ምዝገባ አሠራር በተጨማሪ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንዳንድ አካባቢዎች በዲጂታል ስርዓት በተከናወነው የምዝገባ ስርዓት፣ እስከ ዛሬ፣ ሚያዝያ 15፣ 2018 ድረስ በተሰበሰበው መረጃ መሠረት 50 ሚሊዮን 514 ሺሕ 155 ያህል መራጮች እንደተመዘገቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ፣ በስካይላይት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል፤ ከነዚህ ውስጥ 23,123,426 (46%) ሴቶች እና 27,390,729 (54%) ወንዶች መሆናቸው ተገልጿል።

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የመራጮች ምዝገባ ሒደት በመከታተል አዲስ ከተዋወቀ የዲጂታል ምዝገባ ስርዓት ጋር የተያያዙ፣ የመንግሥት አካላት መራጮችን በግድ እንዲመዘገቡ ያድረጓቸውን ጫናዎች እና በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉት ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ያስከተሉትን የመራጮች ምዝገባ ተግዳሮት አካታ በዚህ ዘገባ አቅርባዋለች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህዳር ወር ባወጣው የመጀመሪያ ዙር የግዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 7 እስከ መጋቢት 7፤ 2018 ይካሒዳል ተብሎ ታቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ያቀዳቸውን ሥራዎች “አከናውኖ መጨረስ ባለመቻሉ”፣ የመራጮች ምዝገባ መጀመሪያው በሁለት ሳምንት እንዲገፋ አድርጓል። በዚሁ መሠረት የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚከናወን አሳውቆ፣ በዚሁ መሠረት ምዝገባው ተጀምሯል። ይህ በእንዲህ እያለ፣ አንድ ወር ለተጠጋ ጊዜ ሲከናወን የቆየውን የመራጮች ምዘገባ እስከ ሚያዝያ 14 እንዲራዘም፣ ቦርዱ መጋቢት 24፣ 2018 ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ወስኗል። የመራጮች ምዝገባ ጊዜ ሰሌዳን ለማራዘም ያስፈለገበትን ምክንያት ሲገልጽ፣ በዲጂታል ስርዓት ሲከናወን በቆየው ምዝገባ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ ተግዳሮቶች እና በትራንስፖርት አቅርቦት ችግር የባከነውን ጊዜ ለማካካስ እንደሆን አስታውቋል። የመራጮች ምዝገባ በድጋሚ እስከተራዘመበት ጊዜ ድረስ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 36.9 ሚሊዮን መሆኑንም ቦርዱ ጨምሮ አሳውቆ ነበር።
በመራጮች ምዝገባ ወቅት በርካታ ተግዳሮቶች እንደነበሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ሲያነሱ ነበር። ከነዚህ ተግዳሮቶች ውስጥ ዘንድሮ ከጀመረው የዲጂታል ምዝገባ ስርዓት፣ በኢትዮጵያ ካለው የፀጥታ እና ደኅንነት ጉዳይ፣ እንዲሁም የአስፈፃሚ አካላት መራጮችን ለምዝገባ የሚያስገድዱ ተግባራት እንደሆኑ ተጠቅሰዋል።
የዲጂታል ምዝገባ ስርዓት ማስተዋወቅ ተግዳሮቶች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በ7ተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎች እና የመራጮች ምዝገባ በዲጂታል ስርዓት ተከናውኗል። የመራጮች ምዝገባው በአዲስ አበባ እና ድሬ ዳዋ የፌዴራል ከተማ መስተዳደሮች እንዲሁም በሐረሪ ክልል ሙሉ በሙሉ በዲጂታል እንደሚከናወን ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ በሌሎቹ ክልሎች ደግሞ በከፊል በዲጂታል ስርዓት እና ባብዛኛው በማኑዋል (በእጅ ጽሑፍ እና መዝገብ) አሠራር እንደሚከናወን ተገልጿል። በዚህም አፋር ክልል ብቸኛው የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ በማኑዋል የተከናወነበት ክልል ሆኗል። ቦርዱ ይህንን ዕቅዱን ይፋ ባደረገባት ወቅት በዲጂታል ስርዓት ምዝገባ የሚከናወንባቸው 16,573 (31%) እና በማኑዋል 36,153 (69%)፣ በድምሩ 52,726 የምርጫ ጣቢያዎች እንደነበሩ በድረገጹ ላይ የታተመው ዝርዝር ያመላክት ነበር።
ሆኖም የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ መጋቢት 4 ቀን 2018 ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በመጀመሪያው የምዝገባ ሳምንት በ52,773 [ከመጀመሪያው ዕቅድ በ47 የሚበልጥ] የምርጫ ጣቢያዎች ላይ 7ኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ እቅድ ይዞ እንደነበር ገልጸው፣ በ46,757 የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁሶች ስርጭት ተከናውኖ እና ጣቢያዎች ተከፍተው የመራጮች ምዝገባ መካሔድ ጀምሯል ብለዋል። ነገር ግን በመጀመሪያው ሳምንት በ6,395 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ አለመጀመሩንም ጨምረው አሳውቀው ነበር። በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ምዝገባው የተካሔደው በ46,352 ቋሚ የምርጫ ጣቢያዎች እና 2,477 ንዑስ ጣቢያዎች ውስጥ መሆኑ ተገልጿል።
ዲጂታል የመራጮች ራስን በራስ ምዝገባ ስርዓት የተከናወነው “ምርጫዬ” በተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ አማካይነት ሲሆን፣ እንደ አማራጭ፣ መራጮች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት በምርጫ አስፈጻሚዎች እገዛ በታብሌት እንደተከናወነም ታውቋል። የመራጮች ምዝገባ በተጀመረ ማግስት፣ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ ራስን በራስ ለመመዝገብ የሚውለውን “የብሔራዊ መታወቂያቸውን የአዲስ አበባ ነዋሪ በሚል ያወጡ ዜጎች ቁጥር ተገማች ከሆነው የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር አንጻር ከፍ ያለ ሆኖ በመገኘቱ፣ ቦርዱ መራጮች ለመመዝገብ የሚያቀርቡት ሰነድ ላይ ተጨማሪ ማጣራት አድርጎ” የመራጭነት ካርዱን ለመራጮች እንደሚለክ ገልጾ ነበር።
በመጋቢት 4ቱ የምርጫ ቦርድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ከኢንተርኔት ተዳራሽነት እና ሌሎችም ችግሮች ሳቢያ የዲጂታል ምዝገባ ስርዓቱ በማኑዋል ሊተካ እንደሚችል ተገልጾ ነበር። ይህንን መግለጫ ተከትሎ፣ የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ባደረገው የመስክ ቅኝት፣ በሐረር ከተማ ሙሉ በሙሉ፣ በድሬ ዳዋ ከተማ ደግሞ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ የዲጂታል ምዝገባው ቆሞ ወደ ማንዋል የምዝገባ ስርዓት መመለሱን ለመመልከት ችሏል።
የዲጂታል ስርዓት ምዝገባው ከ3G በላይ የበይነመረብ ሽፋን ባላቸው አካባቢዎች የሚካሄድ መሆኑን የገለጸው ቦርዱ፣ ቀሪው በተለመደው መንገድ በማንዋል ይካሄዳል ብሎ ነበር። ቦርዱ በመራጮች ምዝገባ ወቅት የኢንተርኔት እና ኔትወርክ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችን በማንዋል መመዝገብ መጀመሩንም የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ መናገራቸው ይታወሳል። ዋና ሰብሳቢዋ “ቦርዱ በዲጂታል መንገድ ለመመዝገብ አቅዶ ነገር ግን አስቸጋሪ ኔትወርክ ባላባቸው የተወሰኑ አካባቢዎች በቀደመው አሠራር (በማንዋል) ምዝገባ እያከናወነ ነው” ብለው ነበር።
ይህንን ተከትሎ በዲጂታል አማራጭ የመራጮች ምዝገባ ሊካሄድባቸው የነበሩ 996 ምርጫ ጣቢያዎች ወደ ማኑዋል መቀየራቸውን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቦርዱ ድረገጽ ላይ ከተጨመረው መረጃ ለመረዳት ችላለች። ቦርዱ በድረገጹ ባጋራው የተስተካከለ መረጃ መሠረት ሙሉ በሙሉ በዲጂታል የመራጮች ምዝገባ እንደሚካሄድባቸው ተገልጾ የነበሩ 20 ምርጫ ክልሎች ላይ ከዲጂታሉ በተጨማሪ የማኑዋልም ምዝገባ መጀመሩን መረጃው ያሳያል። ከነዚህ ውስጥ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙት ሁለቱም የምርጫ ክልሎች ሙሉ በሙሉ የዲጂታል ምዝገባ ማከናወናቸው ቀርቶ በ25 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የማኑዋል ምዝገባ ተጀምሯል። በአጠቃላይ የመራጮች ምዝገባ በዲጂታል አማራጭ ይካሄድባቸዋል ተብለው የታቀዱ 996 የምርጫ ጣቢያዎች ወደ ማኑዋል ተቀይረዋል።
በዲጂታል የመራጮች ምዝገባ ከሚካሄዱባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም የምርጫ ክልሎች፣ በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር አደአ 1 ምርጫ ክልል እንዲሁም በአዳማ ከተማ አስተዳደር አዳማ 1 ምርጫ ክልል ላይ ማኑዋሉ ቀርቶ ሙሉ በሙሉ የዲጂታል የመራጮች ምዝገባ እንደተከናወነም ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል።
መራጮችን እንዲመዘገቡ ማስገደድ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ዜጎች ላይ የምዝገባ ካርድ እንዲወስዱ የሚደረግ ያልተገባ ተፅዕኖ እና ሕገ ወጥ ድርጊቶች እየተፈጸሙ መሆኑን፣ ቦርዱ መጋቢት 24፣ 2018 ባወጣው መግለጫ አስታውቆም ነበር። በተለይም “ቤት ለቤት በመዘዋወር ካርድ ውሰዱ በሚል ሕግን የሚጥስ ተግባር፣ ካርድ ካልወሰዳችሁ” በሚል የማኅበራዊ አገልግሎት እና ደሞዝ ለማግኘት እንደ ቅድመ ሁኔታ የማስቀመጥ ተፅዕኖ እየተደረገ መሆኑን ሪፖርቶች እንደደረሱት ገልጿል።
በዚህም ቦርዱ ማንኛውም አካል ዜጎችን በግዳጅ እንዲመዘገቡ የማድረግ ሥልጣን እንደሌለው በማሳሰብ፣ ይህ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም አዟል። ድርጊቱ በማይቆምባቸው አካባቢዎች ምርጫውን እስከማሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቆም ነበር። “የመራጭነት ካርድ ካልወሰዳችሁ ደመወዛችሁ ይቆረጣል በማለት ማስፈራራት ሕገ ወጥ ድርጊት በመሆኑ ቦርዱ አጥብቆ ይቃወማል” ሲል ነበር ማሳሰቢያውን የገለጸው። ቦርዱ መምረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንጂ ግዴታ አለመሆኑንም አክሎ በመግለጫው ጠቅሷል።
ይህን መሰል ጫናዎች በተለያዩ አካባቢዎች መኖራቸው “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በርካታ ጥቆማዎች የደረሷት ሲሆን፣ ጫናዎቹ እስከ ምዝገባው ማጠናቀቂያ ቀናት ቀጥሎ እንደ ነበር ማሳያዎችን ለማግኝት ሞክራለች። ለአብነትም፣ የተራዘመው የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ አንድ ቀን ሲቀረው፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 ከቀኑ 11:00 አካባቢ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ፣ ሀያት 02 ኮንዶሚኒየም ጣፎ መናፈሻ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ምርጫ በግዳጅ እንዲመዘገቡ መደረጋቸውን ከተመዝጋቢዎች መረዳት ችላለች።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ኃይሌ ጋርመንት አካባቢም አስገዳጅ የመራጮች ምዝገባ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል። በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር፣ ኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ፣ ቱሉዲምቱ ወረዳ አስተዳደር፣ የመንግሥት መዋቅሮች ሚሊሻዎችን ጨምሮ “የምርጫ ካርድ መውሰድ ግዴታ ነው” በማለት ነዋሪዎችን በማስገደድ ሲያስመዘግቡ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በቦታው ተገኝታ ታዝባለች።
እነዚህ የመንግሥት አካላቶች በቱሉ ዲምቱ ወረዳ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶች በር ላይ በመቆም “ምርጫ ካርድ ማውጣት ግዴታችሁ ነው፤ ካላወጣችሁ ግን ኢትዮጵያዊ አይደላችሁም” በማለት ኅብረተሰቡን ሲያስገድዱ ለመስክ ቅኝት የተሠማራው የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ጋዜጠኛ ተመልክቷል።
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ ይህንን ችግር አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ቦርዱ ክትትል አድርጎ የምርጫ ጣቢያ እስከመዝጋት የደረሰባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ይህም ሌሎችን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል ብለዋል።
የመራጮች ምዝገባና የፀጥታ ችግር
የፀጥታ እና መረጋጋት ጉዳይ በዘንድሮው ምርጫ ላይ ትልቅ ጥላ ያጠላ መሆኑ ሲዘገብ ቆይቷል። ቦርዱ ምርጫ የሚካሔድባቸው እና የማይካሔድባቸውን አካባቢዎች በምርጫ ቦርድ ግምገማ መሠረት አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ በማለት መለየቱን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር። በዚህም መሠረት በአረንጓዴ የተመደቡት አካባቢዎች “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ” የሚቻልባቸው ናቸው። በቢጫ የተመደቡት “ከጥንቃቄ ጋር ምርጫ ማካሄድ” የሚቻልባቸው ሲሆኑ፣ በቀይ የተመደቡት ደግሞ “ምርጫን ማካሄድ የማይቻልባቸው” እንደሆኑ ተገልጿል። ይሁን እንጂ እነዚህ አካባቢዎች በይፋ ለሕዝብ አልተገለጹም።
የመራጮችን ምዝገባ ለማካሔድ ቁሳቁሶችን ወደ ምርጫ ክልሎች በማጓጓዝ ሒደት ላይ እክሎች እንደገጠሙትም፣ ቦርዱ ሲገልጽ ሰንብቷል። ከነዚህም ችግሮች መካከል የፀጥታ ችግር አንዱ መሆኑ ተጠቅሷል።
እስካሁን የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ ያልተካሔደበት ክልል ትግራይ ክልል መሆኑን የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች የገለጹ ሲሆን፣ ለ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች “አከራካሪ” በተባሉት አምስቱ የምርጫ ክልሎች፣ ማለትም ሁመራ፣ አዲ ረመጽ፣ ጠለምት፣ ኦፍላ ኮረም እና አላማጣ የምርጫ ክልሎች ውስጥ ያሉ አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባን ጨምሮ ምንም ዓይነት የምርጫ እንቅስቃሴ እየተካሄደ አለመሆኑን የአካባቢው መረዳት ተችሏል። ትግራይን በተመለከተ ቦርዱ አሁንም ዝግጅቱን እንደሚቀጥል የተናገሩት የቦርዱ ሰብሳቢ፣ አስቻይ ሁኔታ ሲፈጠር ምርጫውን በክልሉ እናካሒዳለን ብለዋል። የአከራካሪዎቹን የምርጫ ክልሎች ጉዳይም ወደፊት እናሳውቃለን ብለዋል።
በሰኔ ወር 2013፣ ቀጥሎም መስከረም 2014 ዓ.ም በተካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በፌደራል ደረጃ ካሉት 547 የምርጫ ክልሎች መካከል ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በትግራይ 38 (በሁሉም ምርጫ ክልሎች)፣ በአማራ 19 እና በኦሮሚያ 8 የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ አልተካሄደም ነበር። [ ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




