በባሕር ዳር ከተማ የምርጫ ቅስቀሳ መቀዛቀዙ ተገለጸ

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በባሕር ዳር ከተማ የጎዳና ላይ ቅስቀሳዎችን እስካሁን አለመጀመራቸውን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተመልክታለች። የመራጮች ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰፊ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ በከተማዋ ያለው የምርጫ ድባብ ግን አሁንም የተቀዛቀዘ መሆኑ ተስተውሏል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የባሕር ዳር ቅርንጫፍ አስተባባሪ ለ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አልፎ ገዢው ፓርቲም ቢሆን እስካሁን አንድ ብቻ የጎዳና ላይ ቅስቀሳ እንዳደረገ ታውቋል።

የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ባደረገው የመስክ ቅኝት፣ ብልፅግና ፓርቲ ሚያዝያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ሰፋ ያለ የጎዳና ላይ ቅስቀሳ አድርጓል። በተጨማሪም፣ የተለያዩ መጠን ያላቸውን ፖስተሮችን በመለጠፍ የቅስቀሳ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ተመልክቷል። ከገዢው ፓርቲ ውጪ ግን እንዲህ ያለውን ተግባር ያከናወነ ሌላ ፖለቲካ ፓርቲ አልተስተዋለም።

የከተማዋ ነዋሪዎች የሆኑት ሰንደቁ እንዳላማው እና ሂሩት ዘላለም እንደተናገሩት፣ እስካሁን በከተማዋ ያዩት ምንም ዓይነት የጎዳና ላይ ቅስቀሳ የለም። የድምፅ ማጉያዎችንና በራሪ ወረቀቶችን በመጠቀም በጎዳናዎች ላይ እየተዘዋወሩ የመቀስቀስ ተግባር በገዢው ፓርቲም ቢሆን ከአንድ ጊዜ በላይ ሲከናወን አልታየም።

ይህ የምርጫ ድባብ መቀዛቀዝ በክልሉ ላለፉት ሦስት ዓመታት በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት መካከል ያለው ግጭት በዜጎች ነፃ እንቅስቃሴ እና በፖለቲካ ምኅዳሩ ላይ ካሳደረው ተፅዕኖ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይገመታል። በአማራ ክልል በ6ኛው ምርጫ ወቅት በግጭቶች ሳቢያ በ19 የምርጫ ክልሎች ምርጫ ያልተካሄደ ሲሆን፣ ይህም ከትግራይ ክልል ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ብዙ የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ ያልተካሄደበት ክልል ያደርገዋል።

ዘንድሮም በግጭቱ ሳቢያ በርካታ የክልሉ የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ ላይካሄድ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት፣ በተለይ በአማራ ክልል በምርጫ አስፈፃሚዎች ላይ የግድያ እና የእገታ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ማረጋገጡ ለዚህ ስጋት ተጨማሪ ማሳያ ሆኗል። በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን አንድ የምርጫ አስፈፃሚ የተገደለ ሲሆን፣ በአዊና በዋግ ሕምራ ዞኖች ደግሞ የግድያ ሙከራዎች መፈጸማቸውን ኅብረቱ ገልጿል።

በአዴት የምርጫ ክልል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዕጩ ሆነው የሚወዳደሩት አቶ ይበልጣል አድማሴ፣ ለቅስቀሳው መቀዛቀዝ በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል። አቶ ይበልጣል “ክልሉ በሁለት ሐሳቦች መካከል ያለ” መሆኑን ገልጸው፣ በአንድ በኩል በኃይል መንግሥትን ለመጣል የሚንቀሳቀስ አካል መኖሩን፣ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ኢዜማ መንግሥትን መለወጥ የሚቻለው በምርጫ ነው ብለው የሚያምኑ ኃይሎች መኖራቸውን አስረድተዋል። እነዚህ ልዩነቶች በፈጠሩት ስጋት ምክንያት እንደ ቀደሙት ምርጫዎች በነጻነት ተዘዋውሮ ቅስቀሳ ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

ምንም እንኳ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “በግልጽ የደረሰብን ማስፈራሪያ ወይም ክልከላ የለም” ቢሉም፣ በክልሉ ያለው ሁኔታ ግን ለቅስቀሳው “አስቻይ አለመሆኑን” ዕጩው ጠቁመዋል። የባሕር ዳር ምርጫ ቦርድ አስተባባሪም እስካሁን ማስፈራሪያ ደረሰብኝ ብሎ አቤቱታ ያቀረበ ፓርቲ አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

በጎዳና ላይ ከሚደረግ ቅስቀሳ ይልቅ፣ በባሕር ዳር እና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትኩረታቸውን በመደበኛ እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በማድረግ ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ የ“ምርጫ 2018 ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ታዝቧል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]