‘ሥራችንን ብናስረክብም ደሞዝ እና አበል እየተከፈለን አይደለም’ በሚል የምርጫ አስፈፃሚዎች አማረሩ

በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ ተሰማርተው የነበሩ የምርጫ አስፈፃሚዎች፣ ሥራቸውን በአግባቡ አጠናቀው ቢያስረክቡም የክፍያ መዘግየት ቅሬታ እንደፈጠረባቸው “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተቻቸው የአቤቱታ ደብዳቤዎች አመላከቱ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ “አጠቃላይ በውሉ ያስመዘገቡት መረጃ ላይ የተለያዩ ስህተቶች በማጋጠሙ እና ተጨማሪ የማጥራት ሥራ መሥራት በማስፈለጉ ክፍያው ሊዘገይ ችሏል” ሲል ለ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተቻቸው የቅሬታ ደብዳቤዎች፤ የምርጫ አስፈፃሚዎቹ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ክፍያ ሳይፈጸም መቅረቱ ለችግር እንዳጋለጣቸው ከመጥቀሳቸውም ባሻገር፣ በተሰማሩባቸው የምርጫ ክልሎች በቀጣይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ኃላፊነት እንደማይወስዱ አሳስበዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሌሞ 02 የምርጫ ክልል አስፈፃሚዎች “የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በተራዘመው የ14 ቀን የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ ክፍያ ሳይፈፀም በመቅረቱ ለከፋ ችግር ተጋልጠናል” ብለዋል።

የእዣ 02 የምርጫ ክልል አስፈፃሚዎችም በበኩላቸው “ከባድ የሆነ ሀገራዊ ተልዕኮ በመወጣት፣ የተለያዩ ጫናዎችን በመቋቋም መራጮችን መዝግበን አስረክበናል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የውል ስምምነትቱን ወደ ጎን በመተው የሠራንበትን ክፍያ በጊዜው ባለመክፈሉ ሞራል በሚነካ መልኩ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች በማዘዝ ላይ ይገኛል” ሲሉ ለቦርዱ በላኩት ደብዳቤ ገልጸዋል።

አስፈፃሚዎቹ “ቦርዱ በአፋጣኝ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ” በቀጣይ በምርጫ ክልሉ ለሚፈጠረው ችግር ኃላፊነት እንደማይወስዱም አክለዋል።

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ሌላኛው ማመልከቻ የወናጎ 01 የምርጫ ክልል 46 የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች እና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት “ምንም ዓይነት ክፍያ አልተፈፀመም” የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ነው። በተጨማሪም በቡሌ የምርጫ ክልል የ332 የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች እና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው በመግለጽ፣ “በጊዜ ክፍያ ካልተፈፀመ ብዙ የሥራ መስተጓጐል ችግር ቢፈጠር ምርጫ ክልሉ ኃላፊነት አይወስድም” ብለዋል።

ቦርዱ በበኩሉ በውሉ መሠረት ክፍያዎችን እየፈጸመ መሆኑን ገልጾ፣ ለተወሰኑ አስፈፃሚዎች ግን ለክፍያ መዘግየት ምክንያት የሆኑ ችግሮች እንደገጠሙት ለ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በጽሑፍ አሳውቋል።

ቦርዱ ለክፍያው መዘግየት እንደ ተግዳሮት የጠቀሳቸው ነጥቦች፦ “አስፈፃሚዎች ስማቸውን በትክክል አለማስገባት፣ የተረጋገጠ የባንክ ሒሳብ ቁጥራቸውን አለማስመዝገብ (ክፍያው የባንክ ሲስተም ላይ በሚያልፍበት ወቅት መስተጓጎል በመግጠሙ) ፣ የቤተሰብ የባንክ አካውንት ወይም የሌላን ሰው አካውንት በማስመዝገብ፣ ከባንኩ ጋር ያስተሳሰሩት ወይም አካውንት ያወጡበት ስልክ ቁጥር በአስፈጻሚነት ሲመዘገቡ ካስመዘገቡት የእጅ ስልካቸው ቁጥር ጋር የተለያየ መሆን እና ማጥራት በመጠየቁ” የሚሉ ናቸው።

በተጨማሪም “በዲሲፒሊን ምክንያት የተቀነሱ አስፈፃሚዎች በመኖራቸው፣ የተቀነሱትን እያጠሩ መክፈል የግድ በማስፈለጉ እና በውሉ መሠረት ሥራው መሠራቱን መረጃዎቹን የመሰብሰቡ ሂደት ከገጠራማ እና መኪና ከማይገባባቸው አካባቢዎች ጭምር መሆኑ ክፍያው በወቅቱ እንዳይከፈል ያደረጉት ተግዳሮቶች ናቸው” ብሏል።

ቦርዱ በአጠቃላይ 259,894 አስፈፃሚዎችን በጊዜያዊነት የቀጠረ ሲሆን፣ የአጠቃላይ ክፍያውን 40 በመቶ የመራጮች ምዝገባ በተጠናቀቀ በ15 ቀናት ውስጥ እንደሚፈጽም በውሉ አስፍሮ ነበር። የመራጮች ምዝገባ ለ14 ቀናት መራዘሙን ተከትሎ ቦርዱ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ለምርጫ አስፈፃሚዎች በጻፈው ደብዳቤ ለተጨመሩት ቀናት ክፍያ እንደሚፈጸም አሳውቆ ነበር። ይሁን እንጂ ቦርዱ ለ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጠው ምላሽ ይህ ተጨማሪ ክፍያ በሁለተኛው ዙር ከቀሪው 60 በመቶ ክፍያ ጋር አብሮ እንደሚከፈል ገልጿል።

አስፈፃሚዎቹ በበኩላቸው “የምርጫ አስፈፃሚዎች በተፈራረምነው ውል መሠረት ክፍያ እየተከፈለን ባለመሆኑ የትራንስፖርት እና የምግብ ወጪን ጨምሮ መክፈል ባለመቻላችን በከፍተኛ ስቃይ ላይ እንገኛለን” በማለት ለቦርዱ ማሳወቃቸውን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተመልክታለች።

ከክፍያ መዘግየቱ በተጨማሪ በአስፈፃሚዎች ላይ የደረሰ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖሩን ‘የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ’ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል። በተቃራኒው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ “የምርጫ አስፈፃሚዎች የክፍያ መዘግየትም ሆነ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ደርሶብኛል በሚል የቀረበልኝ ምንም ዓይነት አቤቱታ የለም” ማለቱ ይታወሳል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]