ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በተለይም በ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)ን ወክለው በሚያደርጉት የቲክቶክ ምርጫ ቅስቀሳ በብዙዎች ዘንድ ታዋቂነትን አፍርተዋል። ከሰሞኑ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢሶዴፓ ዕጩዎች መሰረዛቸውን ካሳወቀ ቀናት ብኋላ፣ “ከምርጫው ራሴን ከዕጩነት አግልያለሁ፤ ከኢሶዴፓ አባልነት፣ አመራርነትም መልቀቄን በደብዳቤ አስገብቻለሁ” የሚል መልዕክት በቲክቶክ ገጻቸው በማስተላለፍ ከአምስተኛው የፖለቲካ ፓርቲያቸው በገዛ ፈቃዳቸው መሰናበታቸውን አሳውቀዋል።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተስፋሁን ምልኬን አስገራሚ የፖለቲካ ጉዞ በአጭሩ ታስቃኛችኋለች።
ተስፋሁን ምልኬ በፖለቲካ ተሳትፎ ትንሽ የቆዩ ቢሆኑም፣ ቲክቶክን ተጠቅመው በሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳም ፓርቲያቸው “ምርጫውን ካሸነፈ” ብለው የሚገቧቸው ቃል ኪዳኖች በብዙዎች ዕውቅናን ያተረፉት ዘንድሮ ነው። ከነዚህ ቃል ኪዳኖች ውስጥ የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች የባለቤትነት ካርታ መስጠት፣ የፖሊስ አባላትን የመኖሪያ ቤት ባለቤት ማድረግ፣ እና የዲግሪ ሰርተፊኬትን ማስያዣ በማድረግ የባንክ ብድር ለወጣቶች ማመቻቸት የመሳሰሉት ይገኙበታል።
ከ2009 ጀምሮ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት ፖለቲከኛው፣ መጀመሪያ የተቀላቀሉት ራዕይ ፓርቲን ነበር። ከዚያም በኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፓርቲዎች ውስጥ የሐረሪ ክልል የፓርቲ ተወካይ እና ዕጩ በመሆን እንዲሁም፣ ከ2017 ጀምሮ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በመቀላቀል በዘጠኝ ዓመት ውስጥ ከአምስት ፓርቲዎች ጋር መሥራታቸውን ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
“ለመሆኑ ፓርቲ ለምን ይቀያይራሉ?” ስትል “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ላነሳችላቸው ጥያቄ፣ “የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆን አልፈልግም፤ ፖለቲካ ሃይማኖት አይደለም” በማለት “ይበጃል” ያሉትን ፓርቲ እንደሚመርጡ ተናገረዋል። አክለውም፣ “እኔ ሐሳቤን አልቀይርም። ቢሮ ነው የምቀይረው” ሲሉ ተናግረዋል።
“በተቀላቀልኩባቸው ፓርቲዎች ውስጥ ሚዲያ ላይ ካለው ጉልበት ባሻገር መሬት ላይ ያለው ክንውን ባለመመጣጠኑ፣ የፓርቲዎቹ ህልውና የምርጫ ቦርድ የገንዘብ ድጎማ ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው፣ እንዲሁም ራዕይ ፓርቲ በመክሰሙ፣ ኢዜማ ፓርቲ ደግሞ ዕጩ ሆነን በመንግሥት ታስረን ሊያስፈታን የሚችል ባለመኖሩ፣ አመራር ሆኖ ለመቀጠል ዋስትና እንደሌለን ስረዳ ከፓርቲው ለቅቄ ወጥቻለው” በማለት ለሁሉም ምክንያት እንዳላቸው አስረድተዋል።

“በተሳተፍኩባቸው ፓርቲዎች ውስጥ ሁሉም ለሕዝብ ነው የምታገለው ይላል፤ እንቀላቀላለን፣ እናደራጃለን፣ እንመራለን። በመጨረሻም ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅ የራስ እና የቡድን ፍላጎት ላይ ስለሚያተኩሩ፣ እኔም የፖለቲካ ፓርቲ እንድቀያይርና እንድዋዥቅ ምክንያት ሆኗል” ብለዋል።
በዚህም በርካታ ፓርቲ በመቀያየራቸው “ብልፅግናን የሚፎካከሩ እና ሐረርን የሚወክሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን መፍጠር ችያለሁ” ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ተስፋሁን ምልኬ አክለውም፣ “ሐረሪ ክልል በፌደራል ሁለት የምክር ቤት ወንበር ብቻ ያለው ሲሆን፣ በክልሉ ከማሟያነት በዘለለ ለእነዚህ ሁለት ወንበሮች ግድ ሰጥቶት የሚወዳደር ፓርቲ ባለመኖሩ በክልል ተወካይ ሆኜ ለማስተካከል ብዙ ሙከራዎችን አድርግያለሁ” ብለዋል።
ፓርቲዎች ላይ ጠንካራ ትችት የሰነዘሩት አቶ ተስፋሁን፣ “ለሕዝቡ ‘ነፃ አውጪ ነኝ ብሎ ነፃ ያወጣ አንድም ፓርቲ የለም’፣ ብዙዎቹ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ድጎማ ብቻ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው፣ ኢትዮጵያዊነት እና የአገር ፍቅር ያለው ሕዝቡ ዘንድ እንጂ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አለመኖሩን ታዝቤያለሁ። ፓርቲዎች የራሳቸውን ጥቅም እንጂ የሕዝቡን ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ለማስፈን የሚሠሩ አይደሉም” በማለት ቁጭታቸውን ገልጸዋል።
በተደጋጋሚ እስር እንደሚገጥማቸው የሚገልጹት አቶ ተስፋሁን “የመንግሥት አካላት እኔን አሰሩኝም፣ አላሰሩኝም፣ በእኔ ሕይወት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም” ብለዋል። ይልቁንም፣ “አንድ አመራርን እንደ ትግል ጓድ ቆጥሮ አብሮ መታገል ባለመኖሩ፣ ሁሉም በራሱ አቅጣጫ ስለሚሮጥ፣ ወደ ኋላ እንዳፈገፍግ አድርጎኛል” በማለት ከአሳሪዎቻቸው ይልቅ የጓዶቻቸው አጋር አለመሆን ከተሳትፎ እንደሚያሸሻቸው ገልጸዋል።
ተስፋሁን ከኢሶዴፓ ለመልቀቃቸውም “በዋነኝነት በፓርቲው ውስጥ ያለው የገንዘብ እና የሥልጣን ሽኩቻ” መንስዔ ነው ብለዋል። አቶ ተስፋሁን ከዕጩነት እና ከፓርቲ አባልነት መልቀቃቸውን በቲክቶክ ባሳወቁበት ወቅት፣ ፓርቲው ውስጥ በተነሳ ክፍፍል ሳቢያ ምርጫ ቦርድ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የኢሶዴፓን ዕጩዎች በሙሉ መሰረዙን አሳውቆ ነበር። አቶ ተስፋሁን ግን “የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ምርጫ ከማድረግ አንፃር ካሉበት መሰረታዊ ክፍተቶች ጋር ተዳምሮ ከምርጫው ዕጩነት እና ከፓርቲው ለመልቀቅ ተገድጃለው” በማለት ገልጸዋል።
ከአባልነት እና ከዕጩነት ለመልቀቅ በቃል በተደጋጋሚ ለወራት እንደጠየቁ እና በፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር ዶ/ር ራሔል ባፌ ግፊት አማካኝነት በፓርቲው ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደቆዩ ተናግረዋል፤ አክለውም፣ የሚስተካከሉ ነገሮች ባለመኖራቸው ራሳቸውን ከፓርቲው አባልነት እና ዕጩነት ማግለላቸውን ፖለቲከኛው ተከራክረዋል።
አቶ ተስፋሁን በቲክቶክ ቅስቀሳቸው ቃል ስለገቧቸው ጉዳዮች ሲጠየቁ፣ “እንደ ኢሶዴፓ ፓርቲ ሁሉም ሰው ወደ እኛ ትኩረት እንዲያደርጉ በማሰብ፣ ሕዝቡ በሚገባው ቋንቋ ለየት ባለ መልኩ አቀረብነው እንጂ፣ አብዛኛው የፓርቲ ሐሳብ ነው” ብለዋል። “የተናገርኩት ነገር በሙሉ ከፓርቲያችን ማኒፌስቶ፣ ፕሮግራም አንፃር እንዴት ይተገበራል የሚለው ጉዳይ ታስቦበት እና ታቅዶ ነው” በማለት “ለመመረጥ ብቻ የሚወራ ፕሮፓጋንዳ የለም” ሲሉ የተጋነነ የምረጡኝ ቅስቀሳ አለማድረጋቸውን አበክረው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ራሔል ባፌ በበኩላቸው፣ አቶ ተስፋሁን ምልኬ ለ7ኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ያደረጓቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳዎች የፓርቲውም አቋሞች እንደሆኑ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሚያዝያ 24፣ 2018 ለኢሶዴፓ በጻፈው ደብዳቤ፣ ፓርቲው ለ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ያቀረባቸው ዕጩዎች ከውድድር ውጪ መደረጋቸውን መግለጹ የሚታወስ ነው። ቦርዱ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው በፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ራሔል ባፌ አማካይነት የተመዘገቡት ዕጩዎች በእነ አቶ አጫሞ ቦቄ በቀረበበት ተቃውሞ ሳቢያ ነው።
ቦርዱ በዶ/ር ራሔል አማካይነት በዲጂታል ሲስተም ተመዝግበው ይፋ የተደረጉትን ዕጩዎች በእነ አጫሞ ቦቄ ተቃውሞ ቀርቦበት ወደ ፍርድ ቤት ክርክር እንዲያመራ ማድረጉን ገልጿል። ፍርድ ቤቱም ‘ዕጩዎች የቀረቡበት አግባብ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ተከትሎ አይደለም’ የሚል ውሳኔ በማሳለፉ፣ ምርጫ ቦርድ ሁለቱን ወገኖች ሊያሸማግል ያደረገው ሙከራ ስላልተሳካ አስቀድሞ ይፋ የተደረጉት ዕጩዎች መሰረዛቸውንና ወደ ኅትመት አለመግባታቸውን አሳውቋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአምስት በላይ ፓርቲዎች ላይ ተሳትፎ ያደረጉት ፓርቲ አቶ ተስፋሁን፣ ከዚህ በኋላ “ባለኝ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቅሜ የራሴን ሐሳብና አመለካከት ልገልጽ እችላለሁ። ከምርጫው በኋላ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ቀጣይ መዳረሻዬን የሚወስን ይሆናል” በማለት ቀጣይ መዳረሻቸውን አለመወሰናቸውን ተናግረዋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




