ለመጪው ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ለታቀደው 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች ለአምስት ወራት ያህል ሲያካሂዱት የቆዩት የምረጡኝ ቅስቀሳ ትናንት ግንቦት 19 ቀን በይፋ ተጠናቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ከዛሬ ግንቦት 20 ጀምሮ እስከ ምርጫው ዕለት ድረስ የሚቆየው የጥሞና ጊዜ የተጀመረ ሲሆን፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ፓርቲዎች የቀረውን አጭር ጊዜ ለዝግጅት እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል። “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ካለፈው ጥር 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የነበረውን የቅስቀሳ ሂደት፣ የፓርቲዎችን ተሳትፎ እና ያጋጠሟቸውን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች መሠረት በማድረግ ተከታዩን የማጠቃለያ የዜና ትንተና አዘጋጅታለች።
በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የዘንድሮው የምርጫ ቅስቀሳ ድባብ ካለፉት የምርጫ ዓመታት አንፃር በእጅጉ የተቀዛቀዘ እንደነበር ተስተውሏል። ይሁን እንጂ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ እና ተቃዋሚው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መኪናዎችን እና ድምፅ ማጉያዎችን በመጠቀም የተሻለ የምረጡኝ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ሰንብተዋል። በትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (ትብብር)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል ደግሞ የቅስቀሳው ማጠቃለያ በሆነው በመጨረሻው ሳምንት አካባቢ በጎዳና ላይ እየተንቀሳቀሱ ቅስቀስቀሳዎችን ሲያደርጉ ታይተዋል።
የቅስቀሳው መዝጊያ መርሃ ግብርን በተመለከተ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ማክሰኞ፣ ግንቦት 17 ቀን በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እና በሌሎች ዋና ዋና የአገሪቱ ከተሞች ግዙፍ “የድጋፍ ሰልፎችን” በማካሄድ ዘመቻውን አጠናቋል። በአንጻሩ ኢዜማ የማጠቃለያ መርሃ ግብሩን ትናንት ግንቦት 19 ቀን በአራት ኪሎ አካባቢ ባደረገው የደጋፊዎች ስብሰባ አከናውኗል።
ለተቃዋሚዎች በአዲስ አበባ ሌላው ትልቅ ፈተና የሆነባቸው የከተማ አስተዳደሩ የወረቀት ማስታወቂያዎችን፣ የዕጩዎችን ፎቶግራፎችና ፖስተሮች በየመንገዱ መለጠፍ መከልከሉ ነው። አስተዳደሩ የዲጂታል ማስታወቂያዎችን ብቻ ይፋ ማድረጉ እና ክልከላውን በተላለፉ አካላት ላይ ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር ቅጣት መጣሉ፣ ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም አቅም ለሌላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች አዲስ መዋቅራዊ ማነቆ ሆኖባቸዋል።
በሐረሪ ክልል እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የምረጡኝ ቅስቀሳው በእጅጉ የተቀዛቀዘበት ዋናው ምክንያት የገንዘብ እጥረት መሆኑን ፓርቲዎች ይገልጻሉ። “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው እንደ ሕብር ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) እና ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ያሉ ተፎካካሪዎች ለእንቅስቃሴያቸው መገደብ የምርጫ ቦርድን የገንዘብ ድጋፍ ማነስ እና መዘግየት፣ እንዲሁም የነዳጅ እጥረትን በዋናነት ተጠያቂ አድርገዋል።
ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የበጀት ድለድሉ የዘገየው ፖለቲካ ፓርቲዎች የአካል ጉዳተኛ ዕጩዎቻቸውን ሕጋዊ ማረጋገጫ በወቅቱ ማቅረብ ባለመቻላቸው እና የመረጃ ክፍተት በመኖሩ መሆኑን ሰብሳቢዋ ሜላትወርቅ ኃይሉ አስረድተዋል። “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በፓርቲዎቹ የምርጫ እንቅስቃሴ በኩል ከፍተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ጥገኝነት መኖሩን አስተውላለች።
በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ በቅስቀሳው ሂደት ላይ ከፍተኛ ጫና አሳርፏል። ከገዢው ብልፅግና ፓርቲ በስተቀር፣ የትብብር ጥምረትን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ አስተማማኝ የአደባባይ ቅስቀሳ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ትብብር ቀደም ሲል በማዕከላዊ ጎንደር አዘዞ ክፍለ ከተማ የቅስቀሳ አስተባባሪዎች መገደላቸውን ተከትሎ፣ በአማራ ክልል ሰፊ የሕዝብ ስብሰባዎችን ከማድረግ መቆጠቡን ማሳወቁ ይታወሳል።
በክልሉ ያለው የፀጥታ ስጋት የምርጫ ቅስቀሳዎችን ብቻ ሳይሆን ምርጫውንም ያስተጓጉለዋል ተብሎ ተሰግቷል። ምርጫ ቦርድ በስምንት የምርጫ ክልሎች ምርጫ እንደማይካሄድ ከማሳውቁም ባሻገር፣ ወደ 10 የምርጫ ክልሎች የምርጫ ቁሳቁስ ማድረስ እንዳልተቻለ ገልጿል።
ከብልፅግና ፓርቲ ዕጩዎች ውጪ፣ ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፉክክር ለመፍጠር በሚያስችል መንገድ ያልተመዘገቡበት የኦሮሚያ ክልልም ብልፅግና ፓርቲ ብቻውን ቅስቀሳ ሲያደርግ ሰንብቷል።
ወደ አራቱ አዳዲስ የደቡብ ክልሎች በተለወጠው ቀጠና፣ እንደፉክክሩ ሁሉ ከሌሎች አካባቢዎች በእጅጉ የከፋ ቢሮክራሲያዊ፣ አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ጫናዎች መመዝገባቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታዎች ያመለክታሉ። የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) በጋሞ ዞን የምረጡኝ ቅስቀሳ ለማድረግ በተደጋጋሚ ቢሞክርም፣ በመንግሥት መዋቅር እና በጸጥታ አካላት በተጣለበት ክልከላ ወደ ዞኑ መግባትና የአደባባይ ቅስቀሳ ማድረግ አለመቻሉን ገልጿል። ፓርቲው ትላንት ግንቦት 19 ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ፣ 16 ቢሮዎቹ በኃይል መዘጋታቸውንና የዕጩዎች እስራት መበርከቱን ጠቅሶ የቁጫ ምርጫ ለሁለት ወራት ታግዶ እንዲቆይ ቦርዱን ጠይቋል።
ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት የመንግሥት የጸጥታ አካላት በጋሞ ዞን ዕጩዎቻቸውን በማሰር፣ ከሥራ በመባረርና ደመወዝ በመከልከል ከፍተኛ ወከባ እያደረሱባቸው መሆኑን በይፋዊ መግለጫው አውግዟል። ጎጎት ለፍትሕ እና አንድነት ፓርቲም በበኩሉ በእዣ ወረዳ የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርግበት ወቅት ታርጋ በሌላቸው ሞተሮች በሚንቀሳቀሱ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ከፍተኛ ማዋከብ እንደደረሰበትና በወልቂጤ ከተማም የአዳራሽ ስብሰባ እንዳይሰበስብ መከልከሉንና አባላቱ መዛታቸውን ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።
ኢዜማም በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች በጋሞ፣ በኮሬ፣ በዳውሮ እና በአርባ ምንጭ ዞኖች ያሉ የፓርቲው ዕጩዎች እና አስተባባሪዎች “ያለ ምንም የሕግ መሠረት” ለእስር እና ለእንግልት መዳረጋቸውን በምሬት አስታውቆ ነበር።
በዘንድሮው ቅስቀሳ ወቅት በብሔራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የተመደበላቸውን የነፃ የአየር ሰዓት በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሙሉ ለሙሉ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ለዚህም እንደምክንያት ያቀረቡት የሚዲያ ይዘት ማዘጋጃ የገንዘብ እና የባለሙያ አቅም ማነስን ነው።
ይህንን የመደበኛ ሚዲያ ክፍተት ለመሙላት እንደ ትብብር እና ኢዜማ ያሉ ፓርቲዎች የየራሳቸውን ይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን በመጠቀም ማኅበራዊ ሚዲያን በስፋት ለዲጂታል ቅስቀሳ አዋለዋል። ኢዜማ በተለይ በቲክቶክ አዝናኝ ይዘት ያላቸውን ቪዲዮዎች በመልቀቅ ከወጣቱ ጋር ለመገናኘት ሞክሯል። የትብብር አመራሮች ደግሞ በተለያዩ የበይነመረብ ሚዲያ ቃለ ምልልሶችን በማድረግ እና በማኅበራዊ ሚዲያ የቀጥታ የውይይት ተሳትፎ ሲያደርጉ ታይተዋል።
ፖለቲካ ፓርቲዎች በቅስቀሳ ወቅት የደረሰባቸውን እንግልት፣ ወከባ እና እስር በሚመለከት ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ሲያወጡ የቆዩ ቢሆንም፣ ሚያዝያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የቅድመ ምርጫ ግኝቶቹን ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት፣ እስካሁን ድረስ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ የደረሰበትን የቅስቀሳ ማነቆ አስመልክቶ ለኮሚሽኑ በይፋ ያቀረበው አቤቱታ የለም ብለዋል። [ምርጫ 2018 -ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]



