ነእፓ በአማራ ክልል “የማጭበርበር ተግባራት ተፈፅመዋል” በሚል ምርጫው እንዲደገም ጠየቀ

ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) “በ7ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ሂደት በአማራ ክልል በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች የደረሱ ችግሮች” በሚል ትላንት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው የቅሬታ መግለጫ፣ ከምርጫ ሕግና ሥነ-ሥርዓት ያፈነገጡ ተግባራት መፈጸማቸውን በመጥቀስ ምርጫው እንዲደገም ጠየቀ።

ፓርቲው ባወጣው ባለ ሁለት ገጽ መግለጫ፣ በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን በለጋምቦ፣ በለገሂዳ፣ በከለላ፣ በደብረሲና 1 እና ደብረሲና 2 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በገዢው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የምርጫ ሕግንና ሥነ-ምግባርን የሚጥሱ ተግባራት መፈጸማቸውን አስታውቋል። ፓርቲው በመግለጫው ላይ፦ “የ… መራጮችን ካርድ በነጠላ በመሰብሰብ መራጮች ወደ ቤት እንዲመለሱ ተደርጓል። (ከለላ፤ ለገሂዳ፤ መካነ ሰላም፤ ወግዲ፤ ወግዲ 03፤ አባዬ 02፤ አባዬ 08፤ ለሚ ዉሃ እና ኅሩይ የጮማ ከተማ…) የመራጮች ካርድ በገዢው ፓርቲ ከሕዝብ በመሰብሰብ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሰላም አመልክተው ወጥተዋል በማለት የማጭበርበር ተግባራት ተፈጽመዋል” ሲል ገልጿል።

በተለይም በለጋምቦ ወረዳ “በወረኢሉ ማጠቃለያ 01 ማኅበረ ሰላም ቀበሌ” ትላንት ከቀኑ 9:35 ላይ ድንገት የተኩስ ድምፅ በመሰማቱ መራጮችና ታዛቢዎች አካባቢውን ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸውን ያወሳው መግለጫው፤ “ከአጭር ቆይታ በኋላ ሲመለሱ የገዢው ፓርቲ አስፈጻሚዎች በምርጫ ጣቢያው ውስጥ ተቀምጠው የመራጮች ካርድ በገዢው ፓርቲ ኮሮጆ ሞልተው ጠብቀዋቸዋል። በዚህም የተነሳ በ02 አባይ እና 03 አባይ ቀበሌ ውስጥ ያሉ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎችን ዘግተው የመራጮችን ካርድ ሰብስበው ወስደው ለራሳቸው መርጠዋል” ሲል አስፍሯል።

በተያያዘም በምርጫ አዋጅ 1162 ላይ የቀበሌ አመራሮችና የጸጥታ አካላት ከምርጫ ጣቢያ 500 ሜትር ርቀው እንዲገኙ ይደነግጋል ያለው መግለጫው፣ በቃሉ እና በገርባ ከተማ የሚገኙ ስድስት የምርጫ ጣቢያዎች በሙሉ በሚሊሻ፣ ፖሊስና የቀበሌ አመራሮች ተጽዕኖ ሥር መዋላቸውን ፓርቲው ገልጿል። በቃሉ 2 የምርጫ ክልል የነበሩ የምርጫ ቦርድ ሠራተኞች የብልፅግና ፓርቲ አባል መሆናቸውን የገለጸው ነእፓ፣ አስፈጻሚዎቹ በግልጽ “ብልፅግናን ምረጡ” በማለት የገዢውን ፓርቲ የምልክት ሰሌዳ ሲያመለክቱ መዋላቸውን አመልክቷል።

በደሴ ከተማ የምርጫ ክልሎች ላይም ተመሳሳይ ችግሮች መፈጸማቸውን የጠቀሰው የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ መግለጫ፤ ሕጋዊ የታዛቢነት ሚና ሳይኖራቸው ወደ ጣቢያ የገቡ የገዢው ፓርቲ አመራሮች በመራጮች ላይ ጫና ማድረጋቸውን፣ ወደ ጣቢያ የሚመጡ ዜጎችን ስም በመመዝገብ የምርጫ ምልክታቸውን እንዲያሳዩ ማድረጋቸውን እና “በምስጢር ድምፅ መስጫ ቦታዎች ውስጥ በመግባት የስንዴ ነዶን ምረጡ ማለት” መፈጸሙን ዘርዝሯል።

በሌላ በኩል በባሕር ዳር ከተማ እና በዙሪያው ባሉ የምርጫ ክልሎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ 70 ሕጋዊ የፓርቲው ታዛቢዎች፣ ከምርጫ ቦርድ ሠራተኞችና ከጸጥታ ኃይሎች በደረሰባቸው ክልከላ ሂደቱን እንዳይታዘቡ መደረጋቸውን ፓርቲው ይፋ አድርጓል። “ታዛቢዎቹ እንዳይታዘቡ መከልከል ብቻ ሳይሆን ስድብና ማንቋሸሽም ደርሶባቸዋል። በተጨማሪም የተወሰኑ ሴት መራጮች መጥተው በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሞሉትን እንዲያሳዩ በማድረግና የስነ-ልቦና ተጽዕኖና ትንኮሳ በማድረግ ምርጫቸውን እንዲቀይሩ አስገድደዋቸዋል” ያለው ነእፓ፣ ጉዳዩን በየደረጃው ላሉ የወረዳ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ቢያመለክትም ምንም ዓይነት ምላሽና መፍትሔ አለማግኘቱን ገልጿል።

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ፤ በእነዚህ የምርጫ ክልሎች የተመደቡ የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎች ነፃና ገለልተኛ አለመሆናቸውን በመጥቀስ፤ “የምርጫው ውጤት ተቀባይነት ስለሌለው የምርጫ ቦርድ ጉዳዩን በአስቸኳይ መርምሮ አስፈላጊውን የሕግ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ ጊዜያዊ ውጤት ከመግለጽ እንዲቆጠብ እና ምርጫው እንዲደገም እንጠይቃለን” ሲል አሳስቧል።  (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)