ከትላንት በስቲያ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተከናወነውን 7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ተከትሎ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ባወጣው መግለጫ፣ የዘንድሮው ምርጫ “ዴሞክራሲን አያዋልድም፣ መፍትሔም አይፈይድም” ሲል በጽኑ ወቀሰ።
ጥምረቱ ዛሬ፣ ረቡዕ፣ ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ማንኛውም ዕጩ በትብብሩ ስም ወደ ምክር ቤት ቢገባ ፍጹም ተቀባይነት እንደማይኖረው አስታውቋል።
ፓርቲው “የጨረባው ምርጫ ዴሞክራሲን አያዋልድ፣ መፍትሔ አይፈይድ” በሚል ባወጣው በዚህ ወቅታዊ መግለጫው፣ ወደ ምርጫው የገባው መሠረታዊ የሀገር ችግሮች በንግግር፣ በድርድርና በጥልቅ ውይይት መፍታት እንዳለባቸው በማመንና “ከውጭ ኾኖ ተባለ ከማለት በተጨባጭ ነውሩን ለማጋለጥ” እንደነበር አስታውቋል።
ይሁን እንጂ አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ከነግዙፍ እንከኑ “ከኢሕአዴጋዊ የጥርነፋ ውርስ ባህርይ እና የጥቅለላ አባዜ ያልተላቀቀ፣ በዓይነቱም ኾነ በድርጊቱ በታሪክ ከሚታወቁት የጨረባ ምርጫዎች ያልተለየ” መሆኑ ገሃድ ወጥቷል ሲል ከሷል።
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በመግለጫው ላይ የምርጫውን ሂደትና ውጤት በተመለከተ “ውጤቱ እና በኹሉም አካባቢዎች የተፈጸሙ ችግሮች ገና ተጠቃለው ያልመጡ ቢኾንም በሂደቱ ከቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ ዕለትና የምርጫ ማግስት ኾነን ስናየው ከነግዙፍ እንከኑ፣ ከአሳሳቹ 97% የአስቻይነት ሪፖርትና ትንተና፣ ከኢሕአዴጋዊ የጥርነፋ ውርስ ባህርይ /co-opted/ እና 99.9% የጥቅለላ አባዜና ጉምዥታ ያልተላቀቀ፣ በዓይነቱም ኾነ በድርጊቱ በታሪክ ከሚታወቁት የጨረባ ምርጫዎች ያልተለየ መኾኑ ገሃድ የወጣ ነው” ሲል ጠንካራ ትችት ሰንዝሯል። አክሎም፣ “በቅርብ ታሪካችን እንዳየነው ይኽ ልማድ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ፣ እጅግ የተወሳሰበውንም የሀገራችንን ችግር ከድጡ ወደ ማጡ ከመውሰድ የዘለለ ዴሞክራሲን አያዋልድም፣ መፍትሔም አይፈይድም!” ብሏል።
“ውጤቱም ምንም ቢኾን የትኛውም ዕጩ በትብብሩ ስም ምክርቤት እንዳይገባ” ሲል ያሳሰብ ሲሆን፣ “ቢገባም ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው” በማለት የምርጫውን ውጤት ጥምረቱ እንደማይቀበለው ከወዲሁ አሳስቧል።
ይህም ሆኖ ፓርቲው በጠባቧ ቀዳዳ የቦርዱ ኃላፊዎችና ውስን ድርጅቶች ላደረጉት ጥረት ዕውቅና እንደሚሰጥ የገለጸ ሲሆን፣ “አገዛዙ የሕዝብን ድምፅ እስከሚያከብር ድረስ” ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በቅርቡ ሕዝብን ያሳተፈ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ የተሟላ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
ትብብር በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ እና ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ “አገዛዙ ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር ድርድር ላይ እስከሚቀመጥ ድረስ” ምንም ዓይነት ዕውቅና የሚመስል መልዕክት ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡ በጥብቅ ጠይቋል።
ይህ ካልሆነ ግን ድርጊቱን በኢትዮጵያውያን ላይ እንደተፈጸመ ጥፋት እንደሚቆጥረው “[መንግሥት] ሸብረክ ብሎ ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር እስከሚደራደር ምንም ዓይነት እውቅና የመስጠት የሚመስል መልዕክት ከማስተላለፍ እንዲቆጠብ እንጠይቃለን። ያ ባይኾን በኢትዮጵያውያን ቁስል ላይ እንጨት እንደመስደድ፣ ለንጹሓን እልቂት ቦምብ እንደማቀበል፣ የግፉ አጋፋሪ እና ከኢትዮጵያውያን ጥቅም በተቃራኒ የቆሙ እንደኾነ አድርገን እንቆጥረዋለን” ሲል አስጠንቅቋል።
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የአምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ሲሆን፣ ለ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ 226 ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 827 ዕጩዎች ለክልሎች ምክር ቤቶች፣ በድምሩ 1,053 ዕጩዎችን አቅርቧል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




