ባሳለፍነው ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተከናወነውን 7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ለመቃኘት የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ማግስቱ ድረስ በአዲስ አበባ፣ ሐረር፣ ባሕር ዳር እና ድሬዳዋ ከተሞች ሰፊ የመስክ ቅኝት አድርገዋል። የምርጫው ዕለት ከጠዋቱ 11:00 ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ለ20 ሰዓታት ያህል ከአንዱ የምርጫ ጣቢያ ወደ ሌላው እየተዘዋወሩ ሂደቱን በቅርብ ተከታትለዋል።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎቻችን በየደረሱበት ያገኙትን መረጃ ለአንባቢዎቿ በየሰዓቱ ስታደርስ ውላለች። በዚህ የማጠቃለያ ትንተና፤ ከቅድመ ምርጫው መዋቅራዊ ሁኔታዎች ጀምሮ በምርጫው ዕለት ከተስተዋሉ ረጃጅም ሰልፎች፣ በጋዜጠኞች ላይ ከደረሱ ሕገ-ወጥ ክልከላዎች፣ ከታዛቢዎች ግኝቶች እንዲሁም ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ፓርቲዎች ካቀረቧቸው የከረሩ የክስ መግለጫዎች ጋር የተያያዙ ክስተቶችን በአንድ ጭምቅ እንደሚከተለው እናቀርባለን።
የቅድመ ምርጫ ሂደቱ አጭር ቅኝት
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞች በአብዛኛው የዘንድሮው ምርጫ ከቀደሙት ሁሉ የተቀዛቀዘ እና ውጤቱም ተተንባይ እንደሆነ ይስማማሉ፤ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት በአገር ውስጥ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እና ፖለቲካዊ ጫናዎች ናቸው።
ባለፈው የ6ኛው ምርጫ በትግራይ ጦርነት ምክንያት ምርጫ ያልተካሄደበት የትግራይ ክልል፣ ዘንድሮም ሰላምና መረጋጋት ባለመስፈኑ ምርጫ ሳይካሄድበት ቀርቷል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተለይ በአማራ ክልል ያለው ከፍተኛ የጸጥታ ችግር በስምንት የምርጫ ክልሎች ምርጫ ማካሄድ እንዳልተቻለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል። የአፍሪካ ኅብረት የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንደጠቀሰው በትግራይ፣ በአማራ፣ እና ኦሮሚያ ክልሎች በጸጥታ ስጋት ምክንያት በአጠቃላይ 6,400 የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የድምፅ መስጠት ሂደት ማድረግ እንዳልተቻለ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ምርጫው ከመካሄዱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ የተከሰቱት የፖለቲካዊ ምኅዳሩ መጥበብ ማሳያዎች የምርጫውን ድባብ ገና በዋዜማው አጨልመውት እንደነበር ባለሙያዎች ይናገራሉ። የተሻሻለው የሚዲያ ሕግ ዳግም የመንግሥት አስፈጻሚውን ሥልጣን በሚያሰፋ መልኩ መከለስ፣ የዶቼ ቬሌ (DW) እና የሮይተርስ ወኪል ጋዜጠኞች መታገድ፣ እንዲሁም የዋዜማ እና የአዲስ ስታንዳርድ ሚዲያዎች ምዝገባ መታገድንጨምሮ አራት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጊዜያዊነት መታገዳቸው በሂደቱ ላይ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ጫና አሳድሯል።
የምርጫው እንቅስቃሴ ከተጀመረ በኋላም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በደካማ አቅም ሲንቀሳቀሱ፣ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ በሙሉ አቅም ቅስቀሳ ሲያደርግ ከርሟል።
በአዲስ አበባ የአዳዲስ ፖሊሲዎች ማነቆ መፈጠሩ፣ በተለይም ፖስተሮችን መለጠፍ መከልከሉ ተቃዋሚዎችን ፈትኗል። በመኪና ሞንታርቦ ስፒከሮችን ጭኖ ቅስቀሳ ማድረግ ደግሞ በነዳጅ እጥረት እና በኪራይ ውድነት ሳቢያ ባለመሳካቱ፣ ብልፅግና ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ብቻ የተሻለ ቅስቀሳ ማድረግ ችለዋል።
በምሥራቅ ኢትዮጵያ ያሉ ተቃዋሚዎች ከምርጫ ቦርድ የሚለቀቀው የፋይናንስ ድጋፍ በመዘግየቱ እንደተቸገሩ ሲገልጹ፣ በአማራ ክልል የጸጥታው ሁኔታ ያሳሰባቸው ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን በአደባባይ ለማስተዋወቅ ፍርሃት ገብቷቸው ነበር።
በኦሮሚያ ሰፊ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያላቸው እንደ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ያሉ ፓርቲዎች ፈቃዳቸው እንዳይሰረዝ ለመወዳደር ያህል ብቻ ከ10 ያነሱ ዕጩዎችን በማቅረባቸው ለቅስቀሳ ጥረት አላደረጉም። በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ የዕጩዎች እስርንጨምሮ ከፍተኛ ቢሮክራሲያዊ ማነቆ እንደገጠማቸው ፓርቲዎች ገልጸዋል።
የዕጩዎች ቁጥርም የውድድሩን መዳከም የሚያሳይ ነበር። ለፌደራል መንግሥት ብቻውን መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን የ50%+1 (ከ274 በላይ) ዕጩ ማቅረብ የቻሉት ብልፅግና ፓርቲ እና ኢዜማ ብቻ ሲሆኑ፣ በሁሉም የክልል ምክር ቤቶች መንግሥት መመሥረት የሚያስችል ዕጩ ያቀረበው ገዢው ፓርቲ ብቻ ነው። ተቃዋሚዎች በጥቂቶቹ ክልሎች ብቻ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችሉ የዕጩዎች ቁጥር በማቅረባቸው ከወዲሁ የውድድሩን መዳከም እያመኑ ወደ ምርጫው ገብተዋል።
የምርጫው ዕለት ውሎ
ከረዣዥም ሰልፎች እስከ ባዶ ቤት መቆየት
በድምፅ መስጫው ዕለት ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር እና በሐረር ከተሞች የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በሙሉ በነዋሪዎች ረጃጅም ሰልፎች ተጨናንቀው ውለዋል። ለዚህ መስተጓጎል እና መዘግየት ዋናው ምክንያት በዘንድሮው ምርጫ ሥራ ላይ የዋለው አዲሱ የዲጂታል የመራጮች ምዝገባ ሥርዓት ያስከተለው የአሠራር ክፍተት እንደነበር የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ አረጋግጠዋል።
በሞባይል መተግበሪያ እና በታብሌቶች አማካኝነት ራሳቸውን በዲጂታል መንገድ የመዘገቡ ዜጎች መረጃ በቅድሚያ ወደ ሲስተሙ ቢገባም፣ የዕለቱ የመራጮች ማረጋገጫ ባህረ-መዝገብ (ፕሪንት) ተደርጎ ሲዘጋጅ ግን በአማርኛ አልፋቤት (ከሀ እስከ ፐ) የፊደል ተዋረድን የተከተለ ነበር።
በዚህም ምክንያት መራጮች በካርዳቸው ላይ የተሰጣቸው የተለየ የገጽ ቁጥር ባለመኖሩ፣ እያንዳንዱ መራጭ በመጣ ቁጥር አስፈጻሚዎች ስሙን ለማግኘት ሙሉ መዝገቡን በእጅ ለማገላበጥ በመገደዳቸው በጣቢያዎች ላይ ከባድ መጨናነቅ ሊፈጠር ችሏል።
ይህንን ረጃጅም ሰልፍ ለመቅረፍ እና መራጮች ድምፅ እንዲሰጡ ዕድል ለማመቻቸት ቦርዱ መደበኛውን የምርጫ ማጠናቀቂያ ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት 6፡00 ሰዓት ድረስ እንዲራዘም ወስኗል።
ይሁን እንጂ ከምሽቱ 4 ሰዓት በኋላ የመራጮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ የምርጫ ጣቢያዎች ፍጹም ባዶ መሆን ጀምረዋል። እንደ አብነት፣ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በሚገኘው “የግንፍሌ አናጺ እድር ቤት” ምርጫ ጣቢያ ላይ ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ከምርጫ አስፈጻሚዎችና ከፓርቲ ታዛቢዎች ውጭ አንድም መራጭ ያልተገኘ ቢሆንም፣ ጣቢያው እስከ ሌሊቱ 6:00 ድረስ ባዶውን ክፍት ሆኖ እንዲጠብቅ ተደርጓል።
የድምፅ መስጫ ሰዓቱ እስከ ሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ድረስ መራዘሙ፣ ድምፅ ሰጥተው ያጠናቀቁ ጣቢያዎች እንኳ በሕግ በተቀመጠው ገደብ ምክንያት የድምፅ ቆጠራ ሂደቱን በጊዜ እንዳይጀምሩ ማነቆ ሆኖባቸዋል። በአብዛኞቹ ማዕከላት መራጮች ቀድመው ሥራቸውን ቢያጠናቅቁም፣ የቦርዱ የሥራ ኃላፊዎች “የመራጮች ቁጥር እስኪሞላ ወይም የተራዘመው ሰዓት እስኪያበቃ ድረስ መቆየት አለባችሁ” የሚል መመሪያ በመስጠታቸው አስፈጻሚዎች ኮሮጆዎችን ዘግተው ቆጠራ ለመጀመር ሰዓታትን ለመጠበቅ ተገድደዋል።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 በሚገኘው “በትለምልም እድር ቤት” ምርጫ ጣቢያ እስከ ምሽቱ 2፡30 ሰዓት ድረስ ከተመዘገቡት 1,500 መራጮች መካከል 1,200 የሚሆኑት ድምፅ ሰጥተው ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ወደ ጣቢያው የሚመጣ መራጭ ሙሉ በሙሉ በመቆረጡ አስፈጻሚው ቆጠራ ለመጀመር ለምርጫ ክልሉ ጥያቄ ቢያቀርቡም ውድቅ ተደርጎባቸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በምርጫ ክልል 17፣ ወረዳ 13 በሚገኘው “ላስታ ሥላሴ እድር” ምርጫ ጣቢያ ከምሽቱ 4 ሰዓት በኋላ ምንም መራጭ ባይመጣም፣ የድምፅ ቆጠራ ሂደቱ እኩለ ሌሊት አልፎ ዘጋቢያችን ጣቢያውን ለቅቆ እስከሄደበት እስከ 6 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ድረስ ሳይጀመር መዝግይቱ ተስተውሏል።
በእነዚህ ሰዓታት ውስጥ የምርጫ ጣቢያዎች ባዶ ሆነው በመቆየታቸው፣ ደካማ የብርሃንና የመብራት አቅርቦት በነበረባቸው የድንኳን ጣቢያዎች ላይ አስፈጻሚዎች እራት ሲበሉ እና ቡና ሲጠጡ ለማምሸት የተገደዱ ሲሆን፣ የጸጥታ ኃይሎችም መራጭ በሌለበት ባዶ ጣቢያዎች ላይ በተደጋጋሚ ሲገቡና ሲወጡ ተስተውለዋል።
የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች በምርጫው ማግስት ባደረጉት የመስክ ቅኝት፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ በርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የድምፅ ቆጠራው በማግስቱ ረፋድ ላይ ሲካሄድ አስተውለዋል።
በጋዜጠኞች ላይ የተደረጉ ሕጋዊ ያልሆኑ ክልከላዎች
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎችን ጨምሮ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ላይ ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ እስከ ማግስቱ ድረስ በምርጫ ጣቢያዎችና በአካባቢያቸው በርካታ ሕገ-ወጥ የዘገባ ክልከላዎችና እንግልቶች ደርሰውባቸዋል።
በምርጫው ዋዜማ በመስክ ቅኝት ላይ የነበሩ የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች በልደታ ክፍለ ከተማ የገዢው ፓርቲ ታዛቢዎች “ከበላይ አቅጣጫ እስኪሰጠን” በሚል ሰበብ ዘጋቢዎችን ለደቂቃዎች ያቆዩ ሲሆን፣ በየካ ክፍለ ከተማ ደግሞ የጸጥታ ኃይሎች የጋዜጠኞችን ሕጋዊ መታወቂያዎች ተቀብለው በግል ስልኮቻቸው ፎቶግራፍ በማንሳት በደኅንነታቸው ላይ የስነ-ልቦና ጫና ፈጥረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘገባ ፈቃድ ባጅ እና የተቋማቱ መታወቂያ ያላቸው ጋዜጠኞች በሕጉ መሠረት በምርጫ ጣቢያው 200 ሜትር ንፍቀ ክበብ ውስጥ የመንቀሳቀስና የመዘገብ ሙሉ መብት የነበራቸው ቢሆንም፤ በተግባር ግን በተለይ የፎቶግራፍ እና የምስል ቀረጻ ላይ የበረታ እገዳ ተጥሎባቸዋል።
ቦርዱ ይህንን በተመለከተ፣ በምርጫው ዋዜማ ክልከላዎች መደረጋቸውን በመቃወም ማንኛውም ጋዜጠኛ ምርጫውን የመዘገብ መብት እንዳለው በማስታወስ፣ በተለይ የቦርዱ የዘጋቢነት ዕውቅና ባጅ ያላቸው ጋዜጠኞች በምርጫ ጣቢያው 200 ሜትር ውስጥ ገብተው የመዘገብ መብት እንዳላቸው ለማሳሰብ ተገዶ ነበር። ሆኖም፣ ክልከላው የምርጫው ዕለት እና በማግስቱ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ቀጥሏል።
በዚህም መሠረት በቂርቆስ እና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች የምርጫ ዝግጅትን ሲቀርጹ የነበሩ ጋዜጠኞች በፖሊስ አባላት የተከለከሉ ሲሆን፣ በየካ ክፍለ ከተማ የዓይነ ስውራን ጽሕፈት ቤት ጣቢያ ደግሞ አንድ የምርጫ አስፈጻሚ “ፎቶ ማንሳት አይቻልም፤ አንሱ ከተባለ የፈቀድልህን አካል ጠይቅ” በሚል የዘገባ ሥራውን አስተጓጉሏል። ከእነዚህም ባሻገር በቦሌ ሸገር ሕንፃ ፊት ለፊት በሚገኘው ጣቢያ በማግስቱ ግንቦት 25 ቀን ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶችን ለመዘገብ የሞከሩ የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ የፎቶግራፍ ቀረጻ ክልከላ አስተናግደዋል።
በሌላ በኩል፣ በምርጫው ዕለት ምሽት መራጮች በሌሉበት ባዶ ጣቢያዎችን በፎቶ አስደግፎ ለመዘገብ መሞከር ሌላው ጋዜጠኞችን ለክልከላ የዳረገ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል። በየካ ክፍለ ከተማ “የግንፍሌ አናጺ እድር ቤት” ምርጫ ጣቢያ መራጭ ባለመኖሩ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ብቻ ባዶውን የምርጫ ጣቢያ ከፍተው ይጠብቁ በነበረበት የምርጫው ምሽት ወቅት፣ የብልፅግና ፓርቲ ሁለት ታዛቢዎች “መራጭ በሌለበት ሁኔታ፣ ባዶ ቤት መቅረጽ እና ፎቶ ማንሳት የፈለጋችሁት ለምንድነው?” በሚል ክርክር የ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋዜጠኛን ሥራዋን ከልክለዋታል።
በተመሳሳይ መልኩ የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች ቡድን መሪ ኡሁሩ ኬንያታ ጉብኝት አድርገውበት በነበረው “ፒተር ፓን” የምርጫ ጣቢያ የተገኘው ዘጋቢ፣ በጸጥታ አካላት አማካኝነት ፎቶ ማንሳት ብቻ ሳይሆን በጥበቃ ስም በምርጫ ጣቢያው አጠገብ እንኳ በእግሩ እንዳያልፍ ተደርጓል።
የድምፅ መስጠት ሂደቱ መስተጓጎል
በምርጫው ዕለት ከተመዘገቡት እጅግ ከባድ የሕግ ጥሰቶች መካከል በቡርጂ የምርጫ ጣቢያ የተገኘው የአስፈጻሚዎች ግልጽ ወገንተኝነት አንዱ ነው። በዚሁ የቡርጂ ምርጫ ጣቢያ የተመደቡ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ሕጋዊ ኃላፊነታቸውን ችላ በማለት “በድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ ራሳቸው ምልክት እያደረጉ ድምፅ ሲሰጡ” እጅግ አሳፋሪ በሆነ ድርጊት ላይ እያሉ እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል።
ይህንን ተከትሎ ቦርዱ በአስቸኳይ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ጣቢያው ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ ያደረገ ሲሆን፣ ጥፋተኛ በሆኑት የምርጫ አስፈጻሚዎች ላይም ቦርዱ ተነጋግሮ ጠንካራ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በዕለቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
በምርጫው ዕለት በጸጥታ ስጋት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ሳይከፈቱ ከቀሩት 6,400 የትግራይና ከፊል አማራ ክልል ጣቢያዎች በተጨማሪ፣ ድምፅ አሰጣጥ በጥሩ ሁኔታ ተጀምሮ በነበረባቸው በርካታ አካባቢዎች ላይ ሂደቱ በጸጥታ መደፍረስ ምክንያት በድንገት ለመቋረጥ ተገዷል።
ምርጫ ቦርድ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን በሰጠው መግለጫ መሠረት፤ ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ በጸጥታ ችግር ምክንያት የድምፅ አሰጣጥ የተቋረጠባቸው 143 የምርጫ ጣቢያዎች መሆናቸውን ገልጿል።
ከእነዚህ ውስጥ ቢሎኖፓ የተሰኘው በኦሮሚያ የሚገኘው የምርጫ ክልል የተከሰተውን የጸጥታ ሁኔታ ተከትሎ ምርጫው የተቋረጠ ሲሆን፤ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ በሰጡት ማብራሪያ መሠረት በማግስቱ (ማክሰኞ ግንቦት 25 ቀን) በዚህ አካባቢ ምርጫው እንደሚካሄድ አመልክተው ነበር። በአንጻሩ በኩታበር የምርጫ ክልል ስር ከሚገኙት ጣቢያዎች መካከል በ15ቱ ላይ ድምፅ መስጠት የተቻለ ቢሆንም፣ በአራቱ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ግን በጸጥታው መደፍረስ ሳቢያ ምርጫው ሳይከናወን ቀርቷል።
ቦርዱ እነዚህን በቡርጂ የታዩትን ሕገ-ወጥ አሠራሮች (Irregularities) እና በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ያጋጠሙ የጸጥታ መስተጓጎሎችን በሕግ ባለሙያዎች ጉባኤ በኩል እያጣራ መሆኑን ገልጿል። በዚህም መሠረት ገለልተኛ ሆነው ያልተገኙ አስፈጻሚዎችን ከማሰናበት ጀምሮ በከባድ ጥሰት የታዩባቸውን ጣቢያዎች ውጤት እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስታውቋል።
የታዛቢዎች ይፋዊ መግለጫዎች እና ግኝቶች
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተከናወነውን 7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ለመታዘብ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰማሩ የሲቪል ማኅበራትና የጎረቤት አገራት ጥምረቶች፣ ሂደቱ በአብዛኛው ሰላማዊ በሆነ ድባብ መጠናቀቁንና የመራጮች ምዝገባ በዲጂታል ቴክኖሎጂ መታገዙን በበጎ ጎኑ አንስተዋል።
ይሁን እንጂ በጥናት የተደገፉ በርካታ መዋቅራዊ ክፍተቶችና ስጋቶች በጋራ ሪፖርታቸው ገልጸዋል። የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ ታዛቢ ቡድኖች በአገሪቱ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ፣ እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በከፊል በአጠቃላይ 6,400 የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ሳይከፈቱ መቅረታቸውን ጠቁመው፣ ይህም በምርጫው አጠቃላይ አካታችነት ላይ ትልቅ ክፍተት መፍጠሩን አሳስበዋል።
በተጨማሪም በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ በነበረው ከፍተኛ የቦታ ጥበት የተነሳ መራጮች፣ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ተጠጋግተው ለመቀመጥ መገደዳቸውን በስጋትነት መዝግበውታል።
በሌላ በኩል፣ በአገር ውስጥ 101 አባል ድርጅቶችን በማቀፍ በአጠቃላይ 3,373 ታዛቢዎችን ያሰማራው የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (CECOE)፤ በዕለቱ የተፈጸሙ በርካታ የሕግ ጥሰቶችንና የአሠራር ግድፈቶችን ይፋ አድርጓል።
ኅብረቱ ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት መሠረት፣ በ130 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የመራጮች መዝገብ ላይ ስማቸው ሳይገኝ እና የመራጭነት ካርድ ሳይዙ ከአንድ እስከ 10 የሚሆኑ ሰዎች እንዲመርጡ ተፈቅዶላቸዋል።
ከዚህም በላይ በ161 ጣቢያዎች ላይ መራጮችን ተከትሎ ወደ ምስጢራዊ ክፍል በመግባት የምስጢር የመምረጥ መብት የተጣሰ ሲሆን፤ እጅግ አሳሳቢ በሆነ መልኩ ደግሞ በ77 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ምርጫ አስፈጻሚዎች ራሳቸው በድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ ምልክት ሲያደርጉ መታዘባቸውን በጥናት አስደግፎ አጋልጧል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የከረረ ተቃውሞ እና የድጋሚ ምርጫ ጥያቄዎች
ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ተከታታይነት ያላቸው የክስ መግለጫዎች ወጥተዋል። የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) በቁጫ ምርጫ ክልል የምርጫ አስፈጻሚዎችና የጸጥታ አካላት ከመራጮች እጅ ወረቀት እየነጠቁ ለብልፅግና ድምፅ ሰጥተዋል በሚል ምርጫው “ተጭበርብሯል” ማለቱንና ውጤቱ በፎረንሲክ ምርመራ እንዲጣራ ለቦርዱ በጽሑፍ ክስ ማስገባቱን አስታውቋል።
ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በደቡብ ወሎ፣ በደሴ እና በባሕር ዳር ከተሞች በርካታ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ተፈጽመዋል በሚል በእነዚህ አካባቢዎች ምርጫው እንዲደገም ለሚዲያ ይፋዊ ጥያቄ አቅርቧል።
ኢዜማም በበኩሉ ቢያንስ በአምስት የምርጫ ክልሎች (ባኮ ጋዘር ቁጥር 1፣ ላስካ መደበኛ፣ ቢጣ ጌሻ፣ ፈለገ ሰላም እና ማረቃ ጌና) ውጤትን የቀየሩ ከባድ ችግሮች ተፈጽመዋል በሚል ውጤቱ ተሰርዞ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ለቦርዱ በይፋ አመልክቷል። ፓርቲው ገዢው ብልፅግና ፓርቲ እንደ ማኅበራዊ ጥበቃና የትምህርት ቤት ምሳ ያሉ የመንግሥት የልማት ፕሮግራሞችን ለመራጮች ውሳኔ ማሳደጊያ እና “ድምፅ መግዣ” ስልት አድርጎ ተጠቅሞበታል ሲል በጥብቅ ከሷል።
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ከሁሉም የተለየ ትችት የሰነዘረ ሲሆን፣ ሂደቱን “የጨረባ ምርጫ” ሲል ኮንኖታል። ትብብር ዕጩዎቹ በምርጫው ቢያሸንፉም እንኳ በጥምረቱ ስም ወደ ምክር ቤት እንዳይገቡ አሳስቧል።
ይሁን እንጂ ይህንን ተከትሎ በጥምረቱ ውስጥ ክፍፍል የተስተዋለ ሲሆን፤ የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ (አግን) ፕሬዚዳንት አቶ ምርጫው ስንሻው “ምርጫው ሕዝቡ አሸናፊነቱን ያረጋገጠበት ስኬት ነው” በሚል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡትን መግለጫ ጥምረቱ “የብፌ ፖለቲከኞች ትንኮሳ” ሲል ውድቅ አድርጎታል።
የምርጫ ቦርድ ምላሽ እና የውጤት ማጠቃለል ሂደት
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የምርጫውን ፍትሐዊነትና ሕጋዊ ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ተቋማቸው “የሕግ ባለሙያዎች ጉባኤ” ማቋቋሙን አስታውቀዋል።
ይህ ጉባኤ የተቋቋመው በምርጫው ዕለት የተከሰቱ ኹነቶችን በሕግ ሚዛን መርምሮ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ነው። ሰብሳቢዋ ከምርጫው ቀን በፊት ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ቅሬታ እንዴት፣ ለማንና መቼ መቅረብ እንዳለበት ዝርዝር ገለጻ አድርገው እንደነበር አስታውሰዋል።
እስካሁንም በልዩ ቅጽ ተሞልተው፣ በሰው፣ በቪዲዮና በሰነድ ማስረጃዎች የተደገፉ 47 መደበኛ ቅሬታዎች ለቦርዱ የቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 31ዱ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቀሪዎቹ 16ቱ ደግሞ በግል ዕጩዎች የቀረቡ ናቸው። የቀረቡት ቅሬታዎች ይዘት ሰፊ መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢዋ፣ የፓርቲ ወኪሎች መከልከልን፣ ማስፈራራትን፤ ሕገ-ወጥ ቅስቀሳን እና የምርጫ አስፈጻሚዎችን ግልጽ ወገንተኝነት ያካተቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ቦርዱ እነዚህን ቅሬታዎች ተቀብሎ በማጣራት ላይ መሆኑን ገልጾ፣ በተለይም በቡርጂ የምርጫ ጣቢያ ወረቀቶች ላይ ራሳቸው ምልክት ሲያደርጉ የተገኙ አስፈጻሚዎችን ተከትሎ ጣቢያው እንዲዘጋ ማድረጉን እና በአዲስ አበባ ያሉ የሲቪል ልብስ የለበሱ የመስተዳድር አካላት ከጣቢያዎች እንዲወጡ መደረጉን አረጋግጧል።
ይሁን እንጂ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በአማራ ክልል ምርጫው እንዲደገም ያቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ ግን ቦርዱ ዘንድ የደረሰ ምንም ዓይነት ሕጋዊ የጽሑፍ አቤቱታ አለመኖሩን ሰብሳቢዋ ከዚህ መግለጫቸው አስቀድመው አስተባብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ቦርዱ እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች የሰው ኃይል እጥረት ቢያጋጥመውም ውጤቶችን የማዳመር ሥራ ላይ እንደሚገኝ የገለጸ ሲሆን፤ እስካሁን ከ1,138 የምርጫ ክልሎች ውስጥ የ825ቱን ውጤቶች ማጠናቀቁንና ቀሪው ተጠቃሎ ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በማዕከል ደረጃ ይፋዊ ውጤት እንደሚገለጽ አስታውቋል። በምርጫ ሕጉ መሠረት የምርጫ ክልሎች ጊዜያዊ ውጤት ምርጫው በተካሄደ በአምስት ቀናት ውስጥ መታወጅ ሲኖርበት፤ አገር አቀፍ ይፋዊ ውጤቱ ደግሞ በ10 ቀናት ውስጥ ይፋ እንዲሆን ይጠበቃል። በሕዳር 29፣ 2018 ይፋ የሆነው የቦርዱ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ እንደሚያመለክተው፣ ይፋዊ ውጤቱ ሰኔ 4፣ 2018 እንደሚታወጅ ነው። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




