ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 22 ሚኒስትሮችን ያካተተ አዲሱን ካቢኔ ይፋ አደረጉ

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2019 የ7ኛው የፓርላማ ዘመን 1ኛ ዓመት የመሥራች ጉባዔያቸውን አካሂደው አዲሱን የፌዴራል መንግሥት መሥረታቸውን ተከትሎ፣ በድጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሰየሙት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 28 ቀን 2019 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የአዲሱን ካቢኔ አባላት ሹመት ይፋ አድርገዋል።

ምክር ቤቱ ባካሄደው በዚሁ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህን በድጋሚ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ያቀረቡ ሲሆን፣ የቀረቡት 22 የሚኒስትሮች ሹመቶችም በምክር ቤቱ አባላት አብላጫ ድምፅ ጸድቀዋል።

የዛሬው የሚኒስትሮች ሹመት ይፋ ከመደረጉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ፣ ረቡዕ መስከረም 27 ቀን 2019፣ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 1ኛ ልዩ ስብሰባው የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ማጽደቁ ይታወሳል።

የምክር ቤት አባልና የመንግሥት ተወካይ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በረቂቅ አዋጁ ላይ ባቀረቡት ማብራሪያ መሠረት፣ የአስፈጻሚ አካላት አጠቃላይ ቁጥር በነበረበት 22 ሆኖ እንዲቀጥል ተወስኗል። ይሁን እንጂ ሁለት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንደ አዲስ እንዲቋቋሙ የተደረገ ሲሆን፣ ሌሎች ሁለት መሥሪያ ቤቶች ደግሞ የስያሜ ለውጥ ተደርጎላቸዋል።

በዚህም መሠረት ቀድሞ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የነበረው በአዲሱ “የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር” በሚል፣ እንዲሁም ቀድሞ የቱሪዝም ሚኒስቴር የነበረው “የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር” በሚል እንደ አዲስ ተቋቁመዋል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተብሎ ይጠራ የነበረው “የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር” በሚል፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የነበረው ደግሞ “የሎጂስቲክስ ሚኒስቴር” በሚል አዲስ መጠሪያ እንዲሰጣቸው ተደርጓል።

በዛሬው ዕለት ሹመታቸው ከጸደቀው 22 ሚኒስትሮች መካከል ዘጠኙ (41 በመቶ የሚሆኑት) ሴቶች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም በዛሬው ሹመት ላይ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ ሁለት ሚኒስትሮች ተካተዋል። ከእነዚህም መካከል የቀድሞው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በትምህርት ሚኒስትርነታቸው እንዲቀጥሉ ሲደረግ፣ የአፋር ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አሕዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም ደግሞ አዲሱ የሰላም ሚኒስትር ሆነው ተሰይመዋል።

ከስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኋላ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመርጠው በሚኒስትርነት ሲያገለግሉ ከነበሩት መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር በለጠ ሞላ በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ አልተካተቱም።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡት 22 ሚኒስትሮች መካከል 11ዱ አዳዲስ ተሿሚዎች ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ በፌዴራልና በክልል መዋቅሮች ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የፖለቲካና የሥራ ኃላፊነቶች ላይ ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው።

በተለይ የቀድሞዋ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ከመደበኛ የኮርፖሬት አመራርነት ወጥተው ወደ ካቢኔው በመቀላቀል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል።

በሌላ በኩል በቅርቡ የሥራ ዘመናቸውን እስካጠናቀቁበት ጊዜ ድረስ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት አቶ አወሉ አብዲ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ሆነው የተመረጡትን ወ/ሮ ሙፈሪሐት ካሚልን በመተካት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሆነው ተሰይመዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲ ዋና መሥሪያ ቤት የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ እና የቀድሞ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት አቶ ሳዳት ነሻ፣ ዶክተር ዓለሙ ስሜን በመተካት የሎጂስቲክስ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

አዲሶቹ ተሿሚዎች ቀደም ሲል በነበሩባቸው ተቋማት ያካበቱትን ልምድ ይዘው ወደ ካቢኔው እንዲገቡ የተደረገ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታነት ሲያገለግሉ የቆዩት ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ፣ ዶክተር ካሳሁን ጎፌን ተክተው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ሆነዋል።

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሕዝብ ኢንቨስትመንት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ በረከት ፍስሐጽዮን አዲስ ስያሜ የተሰጠውን የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴርን እንዲመሩ ተሰይመዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመንግሥት ሴክተሮችና ብሔራዊ ፕሮጀክቶች ክትትል ቢሮ ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሁም በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ያገለገሉት ዶክተር አክሊሉ ታደሠ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርን በዋና ዳይሬክተርነት የመሩትና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ኢንጂነር መሐመድ አብዱራሕማን፣ ወደ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የተዛወሩትን ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒን በመተካት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ሆነዋል።

ቀደም ሲል በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ፣ የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙትን ዶክተር አብርሃም በላይን ተክተው የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ሆነው ተሰይመዋል።

ሌሎች አዳዲስ ተሿሚዎች የሆኑት ዶክተር ፍስሐ ይታገሱ አቶ መላኩ አለበልን ተክተው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር፤ ወ/ሮ አለምጸሐይ ጳውሎስ አቶ ሀብታሙ ተገኝን ተክተው የማዕድን ሚኒስትር፤ እንዲሁም ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ተክተው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ካቢኔውን ተቀላቅለዋል።

በአዲሱ የካቢኔ አወቃቀር ውስጥ ቁልፍ የቦታ ሽግሽግ ከተደረገላቸው መካከል የቀድሞዋ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ሆነው የተመረጡትን አቶ አህመድ ሺዴን በመተካት የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው ተመድበዋል። በተመሳሳይ መልኩ የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ፣ የቀድሞዋን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድን በመተካት የአገር መከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሰይመዋል።

በነበሩበት የሚኒስትርነት ኃላፊነት እንዲቀጥሉ ከተደረጉት መካከል ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፣ የፍትሕ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሃና አርዓያስላሴ፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ሀብታሙ ኢተፋ እንዲሁም የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ይገኙበታል። በተጨማሪም የቀድሞዋ የቱሪዝም ሚኒስትር ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ አዲስ አደረጃጀት በተሰጠው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሥር በኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ተደርጓል።

በዚህም መሠረት ዛሬ ሹመታቸው የጸደቀው 22ቱ የሚኒስትሮች ካቢኔ አባላት ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ውጭ ጉዳይ)፣ ዶክተር ፍጹም አሰፋ (ገንዘብ)፣ አቶ መሐመድ እድሪስ (መከላከያ)፣ ወ/ሮ ሐና አርዓያስላሴ (ፍትሕ)፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ (ትምህርት)፣ አቶ አዲሱ አረጋ (ግብርና)፣ ዶክተር መቅደስ ዳባ (ጤና)፣ ዶክተር ሀብታሙ ኢተፋ (ውኃና ኢነርጂ)፣ ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ (ገቢዎች)፣ ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ (ባህልና ቱሪዝም)፣ አቶ አወሉ አብዲ (ሥራና ክህሎት)፣ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ታምሩ (ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ)፣ ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ (ንግድና ቀጣናዊ ትስስር)፣ ዶክተር ፍስሐ ይታገሱ (ኢንዱስትሪ)፣ ወ/ሮ አለምጸሐይ ጳውሎስ (ማዕድን)፣ አቶ ሳዳት ነሻ (ሎጂስቲክስ)፣ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ (ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ)፣ አቶ ሙሳ አደም (ሰላም)፣ ኢንጂነር መሐመድ አብዱራሕማን (ከተማና መሠረተ-ልማት)፣ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (መስኖና ቆላማ አካባቢ)፣ አቶ በረከት ፍስሐጽዮን (ብሔራዊ ስትራቴጂ) እና ዶክተር አክሊሉ ታደሠ (ወጣቶችና ስፖርት) ናቸው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ሹመታቸው የጸደቀው 22ቱ ሚኒስትሮች እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ በዕለቱ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፊት ቀርበው ሕገ-መንግሥታዊ ቃለ-መሐላ ፈጽመዋል።

በተጨማሪም በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቶ አደም ፋራህን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ  የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ አስተባባሪ፣ አምባሳደር በትረ መንግስቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊና የካብኔ ጉዳዮች ሚኒስትር፣ ወ/ሮ እናትአለም መለስን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር፣ እንዲሁም አቶ ፍቃዱ ተሰማ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋል (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)