ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ለ64 የፓርላማ መቀመጫዎች ብቻውን ለምርጫ መቅረቡ ታወቀ

ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በመጪው ግንቦት መጨረሻ በሚደረገው ምርጫ፣ በአምስት ክልሎች በሚገኙ 64 የምርጫ ክልሎች ብቻውን ለፓርላማ እንደሚወዳደር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትላትንናው ዕለት ይፋ ያደረገው ሰነድ አመለከተ። ከእነዚህ የምርጫ ክልሎች ውስጥ አርባ ስድስቱ በኦሮሚያ፣ አስራ አንዱ ደግሞ በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው። 

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የምርጫ ቦርድ ሰነድ፤ በሰባተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ለመወዳደር የዕጩነት ምዝገባ የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ዕጩዎች ዝርዝርን የያዘ ነው። ለፓርላማ እና ለክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ዝርዝር በያዘው በዚህ ሰነድ ውስጥ የሐረሪ እና የትግራይ ክልሎች መረጃ አልተካተተም።

የዕጩዎች መረጃ ይፋ ከተደረገባቸው 10 ክልሎች መካከል በአምስቱ ብቻውን በተወዳዳሪነት የቀረበ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ የለም። በስራቸው ባሉ ሁሉም ምርጫ ክልሎች በእያንዳንዳቸው ከአንድ በላይ ተወዳዳሪ የቀረበባቸው ክልሎች አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ናቸው። 

አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችም በተመሳሳይ መልኩ፤ በሁሉም የምርጫ ክልሎቻቸው ከአንድ በላይ ዕጩዎች ለውድድር ቀርበዋል። አዲስ አበባ ካሏት 23 የምርጫ ክልሎች በሦስቱ ገዢው ፓርቲ ለፓርላማ ዕጩዎችን ባያቀርብም፣ ዘጠኝ ፓርቲዎች ለእነዚህ መቀመጫዎች ተወዳዳሪዎችን ማስመዝገባቸውን የምርጫ ቦርድ ሰነድ ያመለክታል። 

ሁለት የምርጫ ክልሎች ብቻ ባሏት ድሬዳዋ በአንጻሩ፤ ብልጽግና ፓርቲ የወቅቱን የከተማይቱን ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር እና የፓርላማ አባሏን ዶ/ር ቢፍቱ መሐመድን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲወዳደሩ በዕጩነት አቅርቧል። ለእነዚህ የድሬዳዋ የፓርላማ መቀመጫዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር የሚወዳደሩት፣ ስምንት ፓርቲዎች እና አንድ የግል ዕጩ ናቸው።

ገዢው ፓርቲ እንደ ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ በርከት ያሉ ተፎካካሪዎች አብረውት ቢቀርቡም፣ በአምስት ክልሎች በሚገኙ 64 የምርጫ ክልሎች ግን ለፓርላማ የሚወዳደረው ብቻውን ነው። ብልፅግና ፓርቲ ባለፈው ስድስተኛው ዙር ምርጫ በ112 የምርጫ ክልሎች ብቻውን መወዳደሩ ይታወሳል።

በዘንድሮ ምርጫ ብልፅግና ፓርቲ በብቸኛ የፓርላማ ተወዳዳሪነት የቀረበባቸው አብዛኞቹ የምርጫ ክልሎች የሚገኙት በኦሮሚያ ክልል ነው። በክልሉ አንድ ተወዳዳሪ ብቻ ከተመዘገበባቸው 49 ምርጫ ክልሎች ውስጥ በ46ቱ ብልጽግና ፓርቲ ያለ ምንም ተወዳዳሪ ለምርጫ ቀርቧል።

አንድ ተወዳዳሪ ብቻ የቀረበባቸው ቀሪዎቹ የምርጫ ክልሎች፤ መንዲ፣ ደደር 2 እና ኮፈሌ 2 ናቸው። በመንዲ ምርጫ ክልል በብቸኛ ተወዳዳሪነት በግል ዕጩነት የቀረቡት የቀድሞው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ቀጄላ መርዳሳ ናቸው።

ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሆነው የሰሩት አቶ ቀጄላ፣ በሰኔ 2016 ዓ.ም ከስልጣናቸው ከተነሱ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካሪ እንዲሆኑ ተደርገዋል። አቶ ቀጄላ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ካቢኔ ተቀላቅለው የነበሩት በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራውን የኦነግ አንድ አንጃ በመወከል ነበር።

አቶ አራርሶ በዘንድሮው ምርጫ በደደር 2 ምርጫ ክልል ለመወዳደር ተመዝግበው የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን የምርጫ ቦርድ ሰነድ ያሳያል። በግል ዕጩነት የተመዘገቡት አቶ አራርሶ፣ እንደ አቶ ቀጄላ ሁሉ ያለ ምንም ተቀናቃኝ ብቻቸውን ለምርጫ ቀርበዋል። 

ቀሪው የኮፈሌ 2 ምርጫ ክልል ላይ በብቸኛነት የቀረቡት ተወዳዳሪ፤ የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ሰለሞን ታፈሰ ናቸው። በኦሮሚያ ክልል ብቻቸውን እንደ ቀረቡት የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ተመራጭ ሁሉ፣ በአማራ ክልል የሚወዳደሩ የአራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጩዎችም ያለ ምንም ተፎካካሪ በምርጫው ይሳተፋሉ። 

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰኘውን የፓርቲዎች ስብስብ በመወከል በአማኑኤል የምርጫ ክልል ለፓርላማ የሚወዳደሩት አቶ ዮሃንስ ጥላሁን እና በደጋ ዳሞት የምርጫ ክልል ለተመሳሳይ ምርጫ የቀረቡት አቶ ይልቃል አስቻለ፣ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ውስጥ ይገኙበታል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) በመወከል በመሐል ሜዳ የምርጫ ክልል የቀረቡት አቶ ዳምጠው ተሰማም አብሯቸው የሚወዳደር ሌላ ዕጩ የለም።

የነጻነት እና እኩልነት (ነእፓ) የሳይንት 2 ምርጫ ክልል የፓርላማ ተወዳዳሪው አቶ መሐመድ ቡሽራ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የግንደ ወይን ምርጫ ክልል ዕጩው አቶ እንደግ አዳነ፣ በተመሳሳይ በብቸኝነት ለምርጫ የቀረቡ ናቸው። አስራ አንድ የብልጽግና ፓርቲ የፓርላማ ተመራጮችም፤ በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ያለ ተወዳዳሪ በግንቦት መጨረሻ የሚካሄደውን ድምፅ መስጪያ ቀን ይጠባበቃሉ።

ገዢው ፓርቲ በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ ሰባት የምርጫ ክልሎች እንደዚሁ በብቸኛነት ዕጩዎችን ያቀረበ ሆኗል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) የፓርላማ ዕጩ የሆኑት አቶ መኮንን ጎለሣ በካማሺ የምርጫ ክልል ብቻቸውን የቀረቡ ሲሆን፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ የኢዜማው ዕጩ አቶ ዘካሪያስ አንበሴ በዳሰነች የምርጫ ክልል ያለ ተፎካካሪ የምርጫው ተሳታፊ ይሆናሉ። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]