የአራት ፓርቲዎች ግንባር የሆነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በዘንድሮው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደረው ለተሳትፎ ያህል መሆኑን የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ አምዶም ገብረሥላሴ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
መድረክ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲ እና ሉዓላዊነት፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ፣ የአፋር ሕዝብ ለፍትህ እና ዴሞክራሲ የፈጠሩት የአራት ፓርቲዎች ግንባር ነው። ግንባሩ ዘንድሮ በአጠቃላይ 219 ዕጩዎችን ቢያቀርብም ከእነዚህ ውስጥ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲ እና ሉዓላዊነት እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ 7 ዕጩዎችን ብቻ እንዳቀረቡ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።
ዓረና አንድ ዕጩ ሲያቀርብ፣ ኦፌኮ ደግሞ 6 ዕጩዎችን ለ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ያቀረበ ሲሆን፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ደግሞ 150 ዕጩዎችን እንዲሁም የአፋር ሕዝብ ለፍትሕ እና ዴሞክራሲ 89 ዕጩዎችን ማቅረብ ችለዋል።
ሊቀመንበሩ ኦፌኮ እና ዓረና በሚወዳደሩባቸው የትግራይ እና የኦሮሚያ አካባቢዎች ያለው የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ ሳቢያ የዘንድሮው ምርጫ “ከተሳትፎ የዘለለ ትርጉም አይሰጠንም” ብለዋል። በትግራይ ክልል ምርጫ ባለመካሄዱ ምክንያት የመድረክ ሊቀ መንበር ራሳቸው ዕጩ ሆነው መቅረብ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
አቶ አምዶም መድረክ በኦሮሚያም ያለው ሁኔታ ለኦፌኮ ዕጩዎች አመቺ አይደለም የሚል እምነት እንዳለው ገልጸው፣ “በኦሮሚያ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ እንዲሻሻል እና የፓርቲው ጽሕፈት ቤቶችም እንዲከፈቱ የፖለቲካ እስረኞችም እንዲፈቱ ከክልሉ መንግሥት ጋር ለመወያየት ብናቅድም፣ ገዢው ፓርቲ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አልቻለም” ብለዋል።
መድረክ በምርጫ 2002 እና በምርጫ 2007 ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ብቅ ማለት ችሎ እንደነበር የሚታወስ ነው።
አቶ አምዶም ግን “መድረክ አሁንም ጠንካራ ነው” ይላሉ። ፓርቲው በዚህ ምርጫ በሚፈለገው መንገድ ያልተሳተፈው “በፀጥታ ችግር ነው። የታጠቁ ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች በመኖራቸው እና ኃላፊነት ለመውሰድ ስለከበደን ዕጩዎችን ማቅረብ አልቻልንም” ሲሉ አክለዋል።
ሊቀመንበሩ “የኢሕአዴግ እና የአሁኑ ምርጫን ማወዳደር አይቻልም”፤ ያሉ ሲሆን፣ “የአሁኑ የተሻለ ቢመስልም በርካታ ኃይሎች የትጥቅ ትግል እያደረጉ ይገኛሉ። ጫናው ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን ከታጠቁ ኃይሎችም ጭምር ነው” በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል።
“ገዢው ፓርቲ (ብልፅግና) ከኢሕአዴግ የተራራቀ አይደለም። ታጣቂዎች ደግሞ ተጨማሪ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ” በማለት የፀጥታ ስጋቱ በፖለቲካ ምኅዳሩ ላይ ተጨማሪ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል።
ሆኖም፣ ለመድረክ የዕጩዎች ቁጥር ማነስ ምክንያቱ የፀጥታ ችግር ብቻ አይደለም፤ የመድረክ ሊቀ መንበር የዲጂታል ምዝገባ ስርዓቱም እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ አምዶም፣ “በዲጂታል ምዝገባ ምክንያት ዓረና በአዲስ አበባ ከተማ ሦስት ዕጩዎችን ለማስመዝገብ አቅዶ፣ ማስመዝገብ የቻለው ግን አንድ ዕጩ ብቻ ነው” ብለዋል። ዓረና ቀጣይ በትግራይ ክልል ምርጫ የሚካሄድበት ዕድል ከተፈጠረ እንደሚሳተፍ አሳውቀዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ “መድረክ ትልቅ ድርጅት ነው። ስለዚህ አለመሳተፉ ትልቅ ኪሳራ ነው”። የአሁን ተሳትፏቸውንም በተመለከተ “ሕጋዊ ሆኖ ለመቀጠል እንጂ መንግሥት ለመመሥረት አይደለም” በማለት የመድረኩን አቋም አስረድተዋል።
በትግራይ ክልል ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በመድረክ ላይ በተለይ ዓረና ፓርቲ ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ የገለጹት አቶ አምዶም፣ “በክልሉ የጦርነት ድባብ ነው ያለው። ሻቢያ እንደፈለገው ይንቀሳቀሳል፣ ፋኖ እንደፈለገው ይንቀሳቀሳል፣ የሕወሓት ጉጅሌ እንደፈለገው ይንቀሳቀሳል፤ ሰላማዊ ነገር የለም” በማለት ሕወሓት ከሌሎች ኃይሎች ጋር ግንኙነት እንደፈጠረ አመላክተዋል።
ይህም በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አቶ አምዶም ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው አባባል፣ “ሕወሓት ከፋኖ ጋር እየሠራ ነው፣ ከኦነግ ሸኔ ጋርም ጋር ግንኙነት አለው፤ ይሄ ደግሞ የምርጫ ምኅዳሩን ይረብሻል”።
አቶ አምዶም አራቱም የግንባሩ አባል ፓርቲዎች የየራሳቸው ርዕዮተ ዓለም እንዳላቸው ገልጸው፣ እንደ መድረክ ሚዛናዊ ሊብራሊዝም ርዕዮተ ዓለም በጋራ እንደሚያራምዱ ተናግረዋል። አክለውም መድረክ ዴሞክራሲ፣ ነፃ ገበያ እና መልካም አስተዳደርን ማዕከል አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ አስረድተዋል።
መድረክ የምርጫ ቅስቀሳው በሚዲያ ብቻ እንደተገደበ ገልጾ፣ ይህም ይሆነው በፀጥታ እና በገንዘብ ችግር ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። መድረክ እንደ ብዙዎቹ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ በምርጫ ቦርድ የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ነው። አቶ አምዶም፣ “ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚከፋፈለው ገንዘብ ግንባርነትን ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ የገንዘብ ድልድል ነው” በማለት ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል። ግንባሩ ከአባላት መዋጮዎች የሚሰበስብ ቢሆንም፣ “ለቅስቀሳ ግን የሚሆን አይደለም” ብለዋል።
እንደ መፍትሔ “መንግሥት ለፓርቲዎች የሚሰጠውን ገንዘብ መልቀቅ”፣ እንዲሁም “የፀጥታውን ሁኔታ ማስተካከል ይኖርበታል” ያሉት አቶ አምዶም፣ አለበለዚያ “ምርጫው አደገኛ ውጤት እንዳያመጣ እና አገሪቱ የበለጠ የፀጥታ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ” መሥራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል። በመጨረሻም፣ የመድረክ ሊቀ መንበር አቶ አምዶም ገብረሥላሴ “ጠንካራ ፉክክር ተደርጎ፣ ተቀባይነት ያለው ውጤት ይኖራል ብለን አንጠብቅም” በማለት ከ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ፓርቲያቸው የተለየ ውጤት እንደማይጠብቅ ገልጸዋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




