የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዛሬው ዕለት ግንቦት 7፣ 2018 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በሐረሪ ክልል ያቀረበው ዕጩ በሐረሪ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል እና ፍትሓ ብሔር ችሎት መሠረት ከምርጫው ውጪ እንደተደረገበት አሳውቋል።
የፓርቲው መሪ አቶ ኢዮብ መሳፍንት “አሁን ላይ የተከለከለው ዕጩዎቻን ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደር ዕጩ ሳይሆን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደር ነው። ይህ በሐረሪ ሕገ መንግሥትም ያልተከለከለ፣ በፌደራል ሕገ መንግሥትም ዕውቅና ያለው ቢሆንም፣ ይህንን ሁሉ ሕግ ጥሶ ከውድድር እንዲወጣ ተደርጓል” ብለዋል።
“በደም እና በአጥንት ተቆጥሮ የሐረሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርበው የሐረሪ ተወላጅ [ብቻ] ነው በሚል የወሰነው ውሳኔ፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው” ያሉት የፓርቲ መሪ “አስነዋሪ የአፓርታይድ ሕግ ነው” ብለዋል።
ጉዳዩን በምርጫ ጊዜ ለማስጮህ ሳይሆን ጉዳዩ ከክልል ምክር ቤት አልፎ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት መምጣቱ ተገቢ አይደለም በሚል ተቃውሞ ማሰማቱን የፖርቲው ኃላፊዎች ገልጸዋል።
“ምርጫ ቦርድም በዚህ ዕጩ ፋንታ የመብቱ ባለቤት ከሚያደርገው ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ይልቅ፣ ከግለሰቡ ብዙ ማንነት አንዱ የሆነውን የዘውጌ ማንነቱን የሚያሟላ ዕጩ እንድንተካ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት ትዕዛዝ ሰጥቶናል” ሲሉ መግለጫውን በንባብ ያቀረቡት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እዩኤል ሰለሞን ገልጸዋል።
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ 3 አንቀጽ 38 (1) ላይ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፤ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት ወይም አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት” በማናቸውም የመንግሥት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት እንዳለው በግልፅ የሕግ ድጋፍ ተሰጥቶታል።
ፓርቲው በመግለጫው “ምንም እንኳን የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ይህንን በግልጽ ቢደነግግም፣ የሐረሪ ክልል ሕገ መንግሥት ከዚህ ፍፁም በተቃራኒ ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ የሚወዳደሩ አባላት በምርጫው ለመወዳደር የሐረሪ ብሔረሰብ አባልነትን መስፈርት አድርጎ አስቀምጧል” ብሏል ።
በዚህ በክልሉ ሕገ መንግሥት ምክንያት ዕጯችን መወዳደር ባለመቻሉ ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ፍርድ ቤት ወስደነዋል ያለው ኢዜማ፣ ይኼ መፍትሄ የማይሰጠው ከሆነ፣ ፓርቲው በክልሉ ውስጥ ምርጫው ላይ ያለውን ተሳትፎ የሚያጤነው መሆኑን የፓርቲው መሪ አቶ ኢዮብ መሳፍንት ተናግረዋል።
የሐረሪ ሕዝብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት ምዕራፍ 4 አንቀፅ 23 “የሐረሪ ሕዝብ ክልል ምክር ቤት በፌደራል ሕገ መንግሥት ለክልሎች የተሰጠውን ሥልጣን ተግባራዊ የሚያደርግ የክልሉ ከፍተኛ የፖለቲካና የሕግ አውጪነት ሥልጣን ያለው አካል” ነው ይላል።
የክልሉ ሕገ መንግሥት የሐረሪ ሕዝብ ክልል ምክር ቤት ከሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ 14 አባላት እንዲሁም ከሐረሪ ሕዝብ ተወካዮች ጉባዔ 22 አባላት በአጠቃላይ 36 አባላት ያሉት ምክር ቤት ነው።
የሐረሪ ሕዝብ ክልል ምክር ቤት ከጀጎል ምርጫ ክልል 4 አባላት እንዲሁም ከጀጎል ውጪ ካሉት የከተማ ቀበሌዎችና የገበሬ ቀበሌ ማኅበራት ምርጫ ክልሎች የሚመረጡ 18 አባላት በድምሩ 22 አባላት ይኖሩታል። የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አባላት በክልሉ ውስጥና ውጪ በሌላ የኢትዮጵያ ክልሎችና ከተሞች ከሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ጭምር ይመርጣል ሲል የክልሉ ሕገ መንግሥት ይደነግጋል። በዚሁ መሠረት ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ ዕጩ ሆነው መቅረብ የሚችሉት የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች ብቻ ናቸው።
“ለምርጫ የቀረው ጊዜ አጭር ከመሆኑ አንፃር ክርክሩ በምርጫ ሒደታችሁ ላይ ተፅዕኖ አይፈጥርም ወይ?” በሚል ከ“ምርጫ 2018 -ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ኢዮብ ሲመልሱ “በሕጉ ሂደት ውሳኔ የማስቀልበስ አቅም አለን፤ አባላቶቻችን በጀጎል 1 የምርጫ ጣቢያ ቅስቃሳ እንዳያደርጉ በመከልከላቸው እሱ እንደሚጎዳን ተረድተናል። ውሳኔውን ለማስቀልበስ እንሠራለን። እግድ ድረስም በመድረስ በእዛ አከባቢ ምርጫ እንዳይደረግ እስከማራዘም እርምጃ እንዲወሰድ እስከመጨረሻው እንታገላለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ ኢዮብ “ምርጫ ቦርድ ከሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ጋር ክርክር ያደረገ ቢሆንም በቂ ባለመሆኑ መፍትሄ ሊያስገኝልን አልቻለም። ለቦርዱ ጉዳዩን አሳውቀን የነበረ ቢሆንም፣ ቦርዱ ውጤቱን በፀጋ መቀበሉ ቅሬታ ተስምቶናል” ሲሉ አክለዋል።
ፓርቲው ከሐረሪ ክልል ውጪም፣ የምርጫ ዝግጅት ሂደቱ ላይ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በተመለከተ በመግለጫ አካቷል።
“የፀጥታ አካላት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ወጥተው ሕግን ብቻ የማስከበር ግዴታ ቢኖርባቸውም፣ በተግባር ግን ለገዢው ፓርቲ ዓይን ያወጣ ወገንተኝነታቸውን በአደባባይ አሳይተዋል” በማለት ወቅሷል።
ኢዜማ በተጨማሪም “አባሎቼን ማሰር እና ማንገላታታቸው ለዴሞክራሲያዊ ሀገር ግንባታ የምናደርገውን እንቅስቃሴ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ሁለት እርምጃ ወደኋላ እንዲመለስ በማድረግ አሰልቺ እና አታካች እያደረገው ይገኛል” ሲል በመግለጫው ገልጾታል።
በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በጋሞ፣ በኮሬ፣ በዳውሮ እና በአርባ ምንጭ ዞኖች የፓርቲው ዕጩዎች እና አስተባባሪዎች “ያለ ምንም የሕግ መሠረት” አባላቶቹ ላይ እስር እና እንግልት እየደረሰባቸው ነው ብሏል።
ሌላው “ከሕግ አግባብ ውጪ ለብልፅግና መዋጮ በሚል ከደሞዛቸው መቁረጥ በሲዳማ ክልል ካሉ መምህራን አባሎቼ ላይ በተለያዩ ክልሎች ላይ በመራጮች እና በደጋፊዎች ላይ የሚፈፀሙ ዛቻና ማስፈራሪዎች የምርጫውን ተዓማኒነት እና ዴሞክራሲያዊነት እየፈተኑ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊፈቱ ይገባል” ሲል ኢዜማ አሳስቧል።
የሐረሪ ክልል የሚከተለው የምርጫ ስርዓት በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫም ወቅት በሐረሪ ክልል እና በምርጫ ቦርድ የፍርድ ቤት ክርክር ማስነሳቱ ይታወሳል። ምርጫ ቦርድ ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አባላት ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላት በልዩ የምርጫ ጣቢያ እንዲሳተፉ የሚያደርገውን አሠራር በማስቀረቱ በክልሉ ክስ ተመስርቶበት ነበር። በፌዴራል ፍርድ ቤቶች እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት የዘለቀው ይህ ክርክር በምርጫ ቦርድ ተሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ያላቸው የድምፅ አሰጣጥ ልምድ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ተደርጓል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




