አቶ ግርማ ሰይፉ ይህንን የተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ቅዳሜ፣ ግንቦት 8፣ 2018 ምሽት፣ የፓርቲው ዓለም ዐቀፍ ድጋፍ ማኅበር ባዘጋጀው የፓርቲውን የምርጫ ዝግጅት የሚመለከት የበይነ መረብ ውይይት ላይ ነው። አቶ ግርማ ከፓርቲው ደጋፊ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀጥለው ምክር ቤት እንደዚህ አይሆንም ብለው ሲያስቡ”፣ እንዴት ይሁን የሚለው ጥያቄ ላይ “የተወሰነ ንግግሮች ነበሩ” ብለዋል። ይሁን እንጂ ንግግሩ “ድርድር ሊባል የሚችል” አለመሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጥር ወር ለፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ “የኔ እምነት ይኼ ፓርላማ፣ አሁን ካሉ አምስት እና አስር ሰዎች በአምስት እና አስር እጥፍ ያደገ ድምፆች ይሰማሉ ብዬ አምናለሁ፣ እፈልጋለሁም” ብለዋል። አክለውም፣ ፓርላማው፣ “የአንድ ፓርቲ ድምፅ ከሆነ ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም” ካሉ በኋላ፣ ይህ እንዲሆንም “ይኼ መንግሥት ይሁነኝ ብሎ ይሠራዋል፤” በማለት በውጤቱ እንየው በማለት ለጊዜ ፍርድ ትተውታል።
ይህንን ተከትሎም በወቅቱ የኢዜማ መሪ የነበሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለደጋፊዎቻቸው የካቲት 14፣ 2018 ባደረጉት ንግግር “በዚህ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወንበር ተጋርተው የሚሻገሩበት እንጂ እንደድሮው ብልፅግና ፓርቲ 99 በመቶ አሸነፍኩ ብሎ መቀጠል ሀገርን ወደሚፈለገው ዕድገት አያሻግርም” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
በቅዳሜው ውይይት ላይ የፓርቲው ምክትል መሪ አቶ ንጋቱ ወልዴ፣ እንዲሁም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አቶ ግርማ ሰይፉ እና አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን መወያያ መረጃዎችን አቅርበዋል። በፕሮግራሙ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ፒተር የተባሉ በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑ የፓርቲው ደጋፊ ባቀረቡት አስተያየት አዘል ጥያቄ “ከገዢው ፓርቲ ጋር ኢዜማ ቀና ነገር” እንዳለው አስታውሰው፣ “ከታች ያለውን አመራር እንደ ችግር” እንደሚያዩት በማከል፣ “ኢዜማ ተቀላቅሎ መግባትን በተመለከተ ድርድር ማድረግ አስፈላጊ አይደለም ወይ?” በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
ጠያቂው አክለውም፣ “በግልጽም ይሁን ከኋላ የሚደረግ ድርድር ካለ አንድ ክልልን ማስተዳደር ቢኖር፣ ይህ የሚያሳየው ለውጥ ደግሞ ወደ ፊት ሀገርንም ጭምር ለኢዜማ አሳልፎ ለመስጠት የሚቻል ነገር ይኖራል ብዬ አምናለሁ” ካሉ በኋላ፣ “በመሆኑም ምርጫ ላይ ብቻ ከመተማመን ይልቅ ድርድር እንደ አማራጭ የማንሳት ነገር ታያላችሁ ወይ?” ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
ይህንን የአቶ ፒተርን ጥያቄ ተከትሎ በቅድሚያ ምላሽ የሰጡት የኢዜማ ከፍተኛ አመራር አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ድርድር በጀርባ አለ ካልነው በፊትለፊት አለ ማለት ነው። አሁን ብልፅግና የሄደበት ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀጥለው ምክር ቤት እንደዚህ አይሆንም ብለው ሲያስቡ፣ ከዛስ እንዴት ይሁን የሚለው ነገር ሲባል፣ የተወሰነ ንግግሮች ነበሩ። ድርድር ሊባል የሚችል ሳይሆን” ብለዋል።
“በንግግሮቹ ውጤት ነው የተወሰኑ ወንበሮችን ብልፅግና መተው እና ሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወዳድረው ቦታውን መያዝ አለባቸው የሚለው ቦታ ላይ የተደረሰው” ሲሉ ለጥያቄው ምላሽ ሰጥተዋል።
“አንዳንዶቹ ስላልተደራደሩ ሊሆን ይችላል፣ ቢደራደሩም ስላልገባቸው ሊሆን ይችላል፣ ብልፅግና የተዋቸውን ቦታዎችን ብልፅግና አይገባባቸውም፤ ሌሎች ይገቡባቸዋል ማለት ነው። ስለዚህ በተጨማሪ ደግሞ በሚደረጉ ውድድሮች ውስጥ ከብልፅግና ሊወሰዱ የሚችሉ ወንበሮች ይኖራሉ። ስለዚህ እነዚህን የድርድር ውጤቶች አድርገን ልንወስዳቸው የምንችላቸው ይመስለኛል” ብለዋል።
ሌላው የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን በበኩላቸው “ከሰሞኑ ሲነዙ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ ብልፅግና ለኢዜማ ወንበር ለቀቀለት የሚለው ይገኝበታል። ብልፅግና የትኛው ወንበር ላይ መወዳደር እንዳለበት እኛ አንወስንለትም። መወሰን ያለባቸው እነሱ ናቸው፤ መጠ፟የቅም ካለባቸው እነሱ ሆነው፣ ኢዜማ ሊጠየቅ አይገባም” ብለዋል።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መጋቢት 16፣ 2018 የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ዕጩዎችን አስመልክታ በሠራችው ዘገባ የኢዜማ መሪ እና ምክትላቸው በሚወዳዳሩባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ ብልፅግና ፓርቲ ዕጩዎች አለማቅረቡን መዘገቧ ይታወሳል። ዘገባውን ተከትሎ ኢዜማ በተለይ ሌሎችም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩ ሆነው ሳለ፣ የኢዜማ ብቻ በስም መጠቀስ ቅር እንዳሰኘው በደብዳቤ መግለጹም እንዲሁ ይታወሳል።
“ብልፅግና አይወዳደርም ማለት ሌሎች ፓርቲዎች አይወዳደሩም ማለት አይደለም”፣ ያሉት አርክቴክት ዮሐንስ፣ “ብልፅግናም ኢዜማም የማይወዳደርበት ትብብር ለኢትዮጵያ የተባለው ፓርቲ ብቻ የሚወዳደርበት ሁለት ቦታዎች አሉ” ሲሉ ገልጸዋል።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የዕጩዎችን ጉዳይ በተመለከተ በተከታታይ ባቀረበቻቸው ዘገባዎቿ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውድድር ከሚደረጉባቸው 547 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በ75ቱ አንድ፣ አንድ ዕጩዎች ብቻ ያለተወዳዳሪ መቅረባቸውን መዘገቧ ይታወሳል።
ከነዚህ ውስጥ በ65ቱ የምርጫ ክልሎች ውስጥ ብልፅግና ብቻውን በዕጩነት የቀረበባቸው ሲሆን፣ ሁለት የግል ተወዳዳሪዎች እንዲሁም ኢዜማ እና ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት እያንዳንዳቸው ሁለት ተወዳዳሪ የሌለባቸው ዕጩዎች ማስመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው ሰነድ ያመላክታል። በተጨማሪም፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ እና የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) እያንዳንዳቸው ተወዳዳሪ የሌለባቸውን አንድ፣ አንድ ዕጩዎች አስመዝግበዋል።
የቅዳሜ ምሽቱ የበይነ መረብ ውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የፓርቲው ምክትል መሪ አቶ ንጋቱ ወልዴ፣ ፓርቲው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ምንም እንኳን መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለው የዕጩዎች ቁጥር ቢያቀርብም፣ ለማሳካት አቅዶ የገባው ግን ሁለት ነገሮችን መሆኑን ገልጸዋል።
“የመጀመሪያው ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ፣ እንዲሁም የተሻለ የሕዝብ ተወካዮችም ሆነ የክልል ምክር ቤት ዕጩ ወንበሮችን ማሸነፍ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የኢዜማን ድርጅታዊ መዋቅር ማጠናከር ነው” ብለዋል።
ፓርቲው በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ አራት የፓርላማ ወንበሮች ብቻ ማሸነፉን ያስታወሱት ደግሞ አርክቴክት ዮሐንስ ናቸው። አርክቴክቱ “ይህንን በዚህኛው ምርጫ በመለወጥ ባናሸንፍ እንኳን ከገዢው ፓርቲ ጋር አንገት ለአንገት በመሆን የተሻለ ቁጥር ያለው ዋነኛው ተቃዋሚ ለመሆን እንሠራለን” ሲሉ ቃል ገብተዋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




