በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች “ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ናቸው” የተባሉ አካባቢዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ እንደተነሳባቸው ተነገረ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደውና የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተው ውይይት ላይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ምርጫ ለማካሄድ “አስቻይ” ስለመሆናቸው የቀረቡት ሪፖርቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ከፍተኛ ጭቅጭቅ ማስነሳታቸውን በውይይቱ የተሳተፉ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት እንደቀረበለት አረጋግጧል።

ሪፖርቱ የቀረበው ቦርዱ በዘጠኝ ቡድን ባዋቀራቸው የክትትል ቡድኖች ሲሆን፣ በሪፖርቱም ከፀጥታ ሁኔታ በተጨማሪ የየአካባቢዎቹ የፖለቲካ ምኅዳር፣ ፓርቲዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ያላቸው ዕድል፣ የሕዝቡ ተነሳሽነት እና የምርጫ ካርድ አወሳሰድ ሁኔታ ተዳስሰዋል ብሏል። ቦርዱ በዚህ ውይይት ላይ በቀረበው ሪፖርት በአብዛኞቹ አካባቢዎች ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ መኖሩ ቢጠቆምም፣ አሁንም ትኩረት የሚሹ ቦታዎች መኖራቸውን አምኗል።

በውይይቱ ወቅት ቦርዱ የቀረቡለትን ሪፖርቶች በተመለከተ ምላሽ ሲሰጥ “ሪፖርቶችን ወስድን የማጣራት ሥራ ከሠራን በኋላ የምንወስደውን እንወስዳለን፣ የማንወስደውን አንወስድም” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ምንጫችን ጠቁመዋል። አክለውም “አማራ ክልል ላይ የቀረበው ሪፖርት ቡድኑ የሄደበት ቦታ ብቻ ነው የተዳሰሰው። ከተማ ከተማውን ነው ያቀረቡት፣ የገጠሩስ የሚለውን ምላሽ አላገኘንም” ብለዋል። በትክክል ተለይቶ በ“አረንጓዴ፣ በቢጫ እና በቀይ” – ምርጫ ማድረግ የሚያስችሉ (አረንጓዴ)፣ ለጊዜው የማይቻሉ ግን ሊለወጡ የሚችሉ (ቢጫ)፣ እና የማያስችሉ (ቀይ) – የሚለው በግልጽ እንዳልቀረበ የገለጹት እኚሁ አመራር፣ በኦሮሚያ ክልል የቀረበው ሪፖርትም ከአማራ ክልሉ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ትክክለኛ የሚመስሉ ሪፖርቶች የቀረቡት በደቡብ አካባቢ እና በቤኒሻንጉል ክልል እንደነበር የገለጹት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሩ፣ “የአስቻይነት ግምገማው በምርጫ ክልል የተካሄደ ነው። እያንዳንዱ የምርጫ ክልል ምን ዓይነት ሁኔታ ነው ያለው? ከምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኝነት ጋር ያለው ሁኔታ የሚለውን በማስቀመጥ ምክረ ሐሳብ በመስጠት የተደረገ ሪፖርት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ቦርዱ ያቋቋመው ኮሚቴ የመጨረሻ ሪፖርቱን የሚያስገባበት ቀን ትላንት ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. መሆኑን የጠቀሱት አመራሩ፣ ቦርዱ ይህንን ሪፖርት መሠረት በማድረግ በቅርቡ የትኛው አካባቢ አስቻይ እንደሆነና የቱ እንዳልሆነ ይፋ ያደርጋል ብለዋል።

ቦርዱ በበኩሉ ትላንት በማኅበራዊ ድረገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ አምስቱም የቦርድ አመራር አባላት፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የከተማ መስተዳድር ከንቲባዎች፣ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ተቋማት አመራሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት ውይይት መደረጉን ገልጿል። ይሁን እንጂ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሩ አስቻይ ተብለው የቀረቡ አካባቢዎች ከፍተኛ ክርክር ያስነሱ መሆናቸውን ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ደግመው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የሕዳሴ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ሱራፌል እሸቱ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት፣ ወደ ዘጠኝ የሚሆኑ ክልሎች በምልከታው ተዳስሰዋል። ከእነዚህ ውስጥ ሶማሌ፣ አፋር እና ሲዳማ ክልሎች ምንም ዓይነት ቅሬታ የቀረበባቸው አካባቢዎች ባለመሆናቸው ክትትል አልተደረገባቸውም።

ኢንጂነር ሱራፌል በጋምቤላ ክልል ከተጓዘው ቡድን አባላት አንዱ እንደነበሩ ጠቅሰው፣ “በክልሉ ከዚህ ቀደም ሁለት ወረዳዎች ኢታንግ ወረዳ እና የጋምቤላ ልዩ ወረዳ የሚባሉ ቦታዎች ላይ ፓርቲዎች አስቻይ ሁኔታ የለም በማለታቸው ክትትል ተደርጓል” ብለዋል።

በዚህ ክትትልም ባለፉት ሁለት ወራት ገደማ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ቡድኑ በበተነው መጠይቅ ማረጋገጡን የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ “በመጣው ሰላም መሠረት ሕዝቡ ወደ ቦታው ተመልሶ ምርጫ ቦርድም በርካታ ማኅበረሰብ ካርድ እንዳወጣ አረጋግጦልናል። ይህም በአካባቢው ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ ተፈጥሯል” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም “ወደ ጋምቤላ ያቀናው ቡድንም በክልሉ ምርጫ አይካሄድባቸውም ወይም አስቻይ አይደሉም የሚባል ቦታዎች እንደሌሉ አረጋግጧል” ብለዋል።

በክልሉ ካሉ 438 ገደማ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ አስቻይ ላይሆኑ የተባሉትን የኢታንግ ወረዳን ጨምሮ በመጠለያዎች ላይ ጭምር የዳሰሳ ክትትል ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ኢንጂነር ሱራፌል ሪፖርት ከቀረበባቸው ዘጠኝ ክልሎች መካከል በአብዛኞቹ ውስጥ አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸው እንደተመላከተ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በአሶሳ አካባቢ አሁንም ግጭት ያለባቸው ቦታዎች ሪፖርት የቀረበ ቢሆንም፣ በፀጥታ ኃይል እገዛ ምርጫውን ማካሄድ እንደሚቻል የሚጠቁም መረጃ መኖሩን ጠቅሰዋል። “በቁጫ አካባቢ ደግሞ አሁንም ፖለቲካ ፓርቲዎች ውጥረት ማርገብ የሚቻል ከሆነ ምርጫ ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ አለ” ብለዋል።

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ሁለት ሁለት ኮሚቴዎች ወደ ቦታው ተጉዘው አብዛኛው አካባቢ አስቻይ መሆኑ በሪፖርት መቅረቡን የገለጹት ኢንጂነር ሱራፌል፣ ነገር ግን በአማራ ክልል የተወሰኑ ወረዳዎች አስቻይ እንዳልሆኑ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ይህ ማለት ግን የመጨረሻውን የ“አስቻይነት” ምላሽ መስጠት የሚችለው የፀጥታ አካሉ ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል። የተወሰኑ አካባቢዎች በኮማንድ ፖስት ሥር ያሉ በመሆናቸው ማረጋገጫ የሚሰጠው የፀጥታ አካሉ እንደሆነና ኮሚቴው መግባት የማይችልባቸው ግጭት ያለባቸው ቦታዎች ላይ መድረስ እንዳልተቻለ አስረድተዋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]