ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በምርጫ ሂደት “እንከኖች” ሳቢያ ተሳትፎውን በድጋሚ ሊያጤን እንደሚችል አስጠነቀቀ፤ የአማራ እና ኦሮሚያን “የአስቻይነት ሪፖርቶችም” ውድቅ አደረገ

የአምስት ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ በ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ሂደት ላይ “ገዢው ፓርቲ እያደረገው ያለው አፈና እና ወከባ ተባብሶ ቀጥሏል” ሲል ወቀሰ። ቅንጅቱ ዛሬ ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም. በማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እና ባወጣው ይፋዊ የአቋም መግለጫ ሰነድ፣ የታዩ መሠረታዊ እንከኖችና “ሕገ-ወጥ አምባገነናዊ ተግባራት” የማይታረሙ ከሆነ፣ በምርጫው የመሳተፍ ጉዳዩን በድጋሚ ሊያጤነው እንደሚችል አስታውቋል።

የጥምረቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ ጋዜጣዊ መግለጫውን በንባብ ያቀረቡ ሲሆን፣ ጥምረቱ ባወጣው ይፋዊ ሰነድ ላይ በተለይ የምርጫ ቦርድ የፀጥታ ክትትል ቡድን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያደረገውን ግምገማ አጥብቆ ተችቷል።

“በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተንቀሳቀሰው ቡድን 97 በመቶ በላይ አስቻይ ሁኔታ አለ በሚል የቀረበው ሪፖርት የተዛባ እና አሳሳች ነው” ያለው ጥምረቱ፣ በአማራ ክልል በጣት የሚቆጠሩ ከተሞች ካልሆነ በስተቀር፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ከዋና ዋና ከተሞች ወጣ ባሉ አካባቢዎች ፍፁም የምርጫ አስቻይ ሁኔታ እንደሌለ በመግለጫው አመልክቷል።

በዚህም ምክንያት ጥምረቱ የሁለቱን ክልሎች የጥናት ውጤት ውድቅ ማድረጉንና ቦርዱም ሆነ ሕዝቡ ውሳኔውን እንዳይቀበሉት ጥሪ ማስተላለፉን አቶ ጌትነት ገልጸዋል።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጌትነት ወርቁ አክለውም እንደገለጹት፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና እና አካባቢው ባሉ ወረዳዎች በዲጂታል ሲስተም ችግር ምክንያት ብቻ ከ15 በላይ የትብብሩ ዕጩዎች ሳይመዘገቡ ቀርተዋል።

የትብብሩ ዋና ጸሕፊ ምሥጢረሥላሴ ታምራት እንደተናገሩት፣ በጠቅላላው በሀገሪቱ የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓት መስተጓጎል ሳቢያ ከ255 እስከ 300 የሚደርሱ ዕጩዎቹ ከውድድር ውጪ እንዲሆኑ ተደርጓል።

ይህ አሠራር “ገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ፍላጎት ለመጫን እና የምርጫውን ሂደት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር” ያደረገው ተግባር እንደሆነ በጥምረቱ መግለጫ ላይ ተገልጿል። በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረጃርሶ ምርጫ ክልል የሚገኙ 92 ምርጫ ጣቢያዎች አፈፃፀማቸው “በአንድ ቦታ በአንድ ድንኳን” ሥር እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ ጌትነት ቅሬታቸውን ሰንዝረዋል።

ጥምረቱ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ሰነድ ላይ፣ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ በርካታ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ዘርዝሯል። ለአብነትም፣ በአማራ ክልል እና በሌሎች አካባቢዎች አንድ መራጭ እስከ አምስት የምርጫ ካርድ እንዲወስድ ተደርጓል ያለ ሲሆን፣ ጥምረቱ ባደረገው ማጣራት አንድ ግለሰብ ሁለት ካርድ የወሰዱበት ማረጋገጫ በእጁ እንደሚገኝ ገልጿል።

የመንግሥት ሠራተኞች፣ ደንብ አስከባሪዎችና የፖሊስ አባላት በየቤቱ በመግባት የመራጮችን ፎቶግራፍ በማንሳት የሥነ ልቦና ጫና እያደረሱባቸው ይገኛልም ሲል ወቅሷል። በአንዳንድ የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም) ኮሚቴዎች አማካኝነት ከነዋሪው ገንዘብ እየተሰበሰበ ለምርጫ አስፈፃሚዎች የምሳ እና የእራት ግብዣ እንዲያደርጉ መገደዳቸውን አቶ ጌትነት ወርቁ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል።

እንደ ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሁሉ፣ ጥምረቱ በሐረሪ ክልል ጀጎል ምርጫ ክልል ያቀረበው የክልል ምክር ቤት ዕጩ “የብሔረሰቡ ተወላጅ አይደለም” በሚል በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደተሰረዘበት አቶ ጌትነት አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ ይህንን ውሳኔ በጥምረቱ ሰነድ ላይ “ጥቁር በጥቁር ላይ የፈፀመው የአፓርታይድ ማሳያ” ሲል ቢኮንነውም፣ ትብብሩ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለመቀበል መገደዱንና ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንደማይወስደው ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በይፋ አረጋግጧል።

ጥምረቱ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያነሳው ከምርጫው “ራሴን አገላለሁ” የሚለው መግለጫ ጥያቄዎችንና ክርክሮችን ሲያስነሳ የቆየ መሆኑን ተከትሎ፣ የጥምረቱ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ጌጡ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ፕሬዝዳንቱ ሲናገሩ “በምርጫው የመሳተፍ ያለመሳተፋችንን ሁኔታ የሚወስነው የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ነው እንጂ፣ በአንድ ፓርቲ ውሳኔ ላይ የተንጠለጠለ አይደለም” ካሉ በኋላ፣ “በትግል ሂደት ውስጥ የምናገኘውን እና የምናጣውን በየግዜው በመገምገም የሚሄድ እንጂ በአንድ ግዜ የሚወስን አይደለም” ብለዋል።

የትብብሩ ዋና ጸሐፊ ምስጥረሥላሴ ታምራት በበኩላቸው፣ “የምርጫው አስቻይነት ጥያቄን ምርጫው 13 ቀን ሲቀረው አይደለም መናገር የጀመርነው” ካሉ በኋላ፣ “ትብብሩ ሲቋቋም ጀምሮ፣ እንዲሁም ፓርቲዎቹ በተናጥልም ጭምር በተደጋጋሚ ገልጸናል” በማለት፣ የመሳተፍ ጉዳይን ማጤን ለማስፈራራት የተባለ እንዳልሆነና እስከ መጨረሻው ድረስ ያለውን ሁኔታ እንደሚገመግሙ አስታውቀዋል።

አቶ ጌትነት ወርቁም ይህንኑ ሐሳብ በማጠናከር፣ “አንደኛው ተመርጠን መንግሥት መሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ የትግል አካል ነው” በሚል ምርጫውን ለሁለት ዓላማ እንደሚጠቀሙበት ገልጸው፣ ጥምረቱ ለዕጩዎቹ ደኅንነት ሲል በአማራ ክልል ካሏቸው 170 ገደማ ዕጩዎች መካከል ለአንዱም እንኳ ቅስቀሳም ሆነ ባነር አለመለጠፋቸውን በቁጭት ተናግረዋል።

የመላው ኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሚያዚያ 30 ቀን ጠርቶት ስለነበረውና ከጥምረቱ ጋር በጋራ ስለሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ አዲስ ነገር መኖሩን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ላቀረበችው ጥያቄ፣ ፕሬዝዳንቱ አቶ አብርሃም ጌጡ “ሰላማዊ ሰልፉ አሁንም ቢሆን አልቀረም። ነገር ግን ሌሎች ኃይሎች በሚፈልጉት መንገድ ወይንም በታቀደልን መንገድ ሳይሆን እኛ ባቀድነው መንገድ ይከናወናል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጥምረቱ ባወጣው መግለጫ ማጠቃለያ ላይ ለገዢው ፓርቲ፣ ለምርጫ ቦርድ እና ለሕዝብ ጥሪ አስተላልፏል። ለገዢው ፓርቲ ባስተላለፈው ጥሪ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና ሁለንተናዊ ድርድር እንዲጀመር የጠየቀ ሲሆን፣ ለቦርዱ ደግሞ የአባላቱን ደኅንነት እንዲያስጠብቅ አሳስቧል። ለሕዝብ ባስተላለፈው መልዕክትም “ድምፅ ሲሰጥ ከጠረጴዛ በታች ማንም እንደማያየው ማወቅ አለበት” በማለት ሕዝቡ ሰላማዊ ትግሉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]