ግንቦት 24፣ ቀን 2018 ዓ.ም. የተካሄደው የኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ፣ በአንዳንድ የኦሮሚያ እና አማራ አካባቢዎች በፀጥታ መታወክ ሳቢያ 143 የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ከጀመሩ በኋላ እንዲያቋርጡ መገደዳቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገልጾ ነበር። ይሁንና የተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ዝርዝር ይፋ አልተደረገም።
ይህ በእንዲህ እያለ፣ አንዳንድ ግጭት የሚያጠኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሁለቱ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች፣ ምርጫውን ለማስተጓጎል ያደረጓቸውን ሙከራዎች ዝርዝር ትንታኔ ማውጣት ጀምረዋል።
ክሪቲካል ትረትስ ፕሮጀክት (ሲቲፒ) እና የትጥቅ ግጭቶች ቦታ እና ሁኔታ መረጃ (አክሌድ) የተባሉ ሁለት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያወጧቸው የዳሰሳ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ በምርጫው ዕለት በመንግሥት እና በትጥቅ ባነገቡ ብሔረተኛ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት፣ የጸጥታ መዋቅሩን ክፉኛ ፈትኖታል።
ሲቲፒ (CTP) ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ በምርጫው አብላጫ ወንበር ያሸንፋል ተብሎ ቢጠበቅም፣ የምርጫው አካታችነት ግን በጥያቄ ውስጥ የወደቀ ነው። ዘገባው ፌዴራል መንግሥቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተቃዋሚዎችን ከውድድር ውጭ አድርጓል ሲል የከሰሰ ሲሆን፣ ለዚህም በግንቦት 2017 ሕጋዊ ሰውነቱ የተሰረዘውን ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)፣ እንዲሁም የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባላት ላይ ተፈፅመዋል ያላቸውን እስራቶች በምሳሌነት አስቀምጧል።
በተጨማሪም፣ ከአፍሪካ ኅብረት (AU) እና ከኢጋድ (IGAD) ታዛቢዎች ውጭ ያሉ ዓለም አቀፍ ነፃ ታዛቢዎችና ገለልተኛ ሚዲያዎች ሂደቱን አለመታዘባቸውን ጠቅሷል።

(የምስሉ ማብራሪያ፤ አክሌድ እንደዘገበው ግንቦት 24፣ የምርጫው ዕለት ከየትኛውም ጊዜ የበለጠ የግጭት ሁኔታዎች ተመዝግበዋል)
የአክሌድ (ACLED) ከፍተኛ ተንታኝ ዶክተር ጃለሌ ጌታቸው ብሩ ባቀረቡት መረጃ መሠረት፣ የድምፅ መስጫው ዕለት (ግንቦት 24 ቀን) በአማራ ክልል በፋኖ ሚሊሻ እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ውጊያ የተስተዋለበት ነበር።
“የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ” የሚባለው ቡድን ምርጫውን ለማስተጓጎል “ኦፕሬሽን አይሻ ሰኢድ” የተሰኘ ጥቃት የከፈተ ሲሆን፣ በዕለቱ ብቻ ቢያንስ 90 ትጥቅ አዘል ግጭቶች ተመዝግበዋል ብሏል። ይህም ከሁለት ዓመት በፊት በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በአንድ ቀን ውስጥ የተመዘገበ ከፍተኛው የውጊያ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል።
በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የተዘጉ የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን ምርጫ ቦርድ የጠቀሰ ቢሆንም፣ የትኞቹ አካባቢዎች እንደሆኑ ዝርዝር አልሰጠም ነበር።
አክሌድ፣ በሰሜን ጎንደር አርባያ አካባቢ ፋኖ ሦስት የምርጫ አስፈጻሚዎችን አግቶ እንደነበር የጠቀሰ ሲሆን፣ በደቡብ ወሎ ኩታበር አካባቢ በተቀሰቀሰው ውጊያ ደግሞ ምርጫው ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ እንደነበር በካርታ አስደግፎ አሳይቷል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ፣ ወይም በተለምዶ አጠራሩ ኦነግ ሸኔ) ከግንቦት 21 እስከ ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚቆይ የመንገድ እገዳ ጥሎ እንደነበረ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በምርጫው ዕለት በምሥራቅ ወለጋ ዞን ላይ ያተኮሩ ቢያንስ 8 የታጠቁ ግጭቶች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር መካሄዳቸውን ሪፖርቶቹ ዘግበዋል።
ኦነሠ በያማ ሎጊ ግርጌ በሚገኙ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ የመንግሥት ኃይሎች በወጡበት ወቅት መግባቱን አስታውቋል ሲል አክሌድ ዘግቧል።
በትግራይ ክልል በፌዴራል መንግሥቱ እና በሕወሓት መካከል ባለው የፖለቲካ ውጥረት ምክንያት ምንም ዓይነት ምርጫ ሳይካሄድ ቀርቷል።
ሕወሓት በፌዴራል መንግሥቱ የሚደገፈውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በማግለል የቅድመ ጦርነት ክልላዊ መንግሥቱን እና አዲስ ካቢኔን በግንቦት እና ሰኔ ወር 2018 ዓ.ም. መልሶ አዋቅሯል። ምርጫ ቦርድ በትግራይ ምርጫ ያላካሄደው ከዚህ ውጥረት በመነጩ “አስቸጋሪ ሁኔታዎች” የተነሳ መሆኑም ይታወቃል።
ሲቲፒ (CTP) ባደረገው ትንበያ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዚህ ምርጫ በኋላ የሚኖራቸውን ድል በሀገር ውስጥ ሥልጣንን ይበልጥ ለማማከል እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ የባሕር በር ተደራሽነትን እና የዓባይ ወንዝ አጠቃቀምን የመሰሉ ቀጠናዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማስፈጸሚያነት እንደሚሆን ግምቱን አሳልፏል።
ይሁን እንጂ የሀገር ውስጥ የታጠቁ ኃይሎች “ፅምዶ” (Tsmido) የተሰኘ ፀረ-መንግሥት ጥምረት ለመፍጠር እየተወያዩ መሆኑን እና እንደ ግብፅ እና ኤርትራ ያሉ የጎረቤት ሀገራት በቪዲዮና ወታደራዊ ስምምነቶች ኢትዮጵያን ለመያዝ የሚያደርጉት ጥረት በቀጠናው የከረረ የጦርነት ስጋት መጋረጡን ሪፖርቱ በስፋት አስገንዝቧል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




