



በኢትዮጵያ በአምባሳደርነት ያገለገሉ 4 የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በሰኔ 2011 በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ውይይት በሀገሪቱ በሚቀጥለው ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ስለሚጠበቀው ምርጫ ተጠይቀው የየራሳቸውን አስተያየት አካፍለዋል። በአሜሪካ የሰላም ኢንስቲትዮት አዘጋጅነት በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው ውይይት ጠንከር ያለ ሀሳብ ያነሱት ዴቪድ ሺን ናቸው።
ሺን ኢትዮጵያ “ምርጫ ለማካሄድ ዝግጁ አይደለችም” የሚል ዕምነት ያላቸው ይመስላል። ዶናልድ ቡዝ ኢህአዴግ ከምርጫ 97 ወዲህ ባልተጠበቀ ውጤት ዳግም መደንገጥ እንደማይፈልግ አስታውሰው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መምጣት ወዲህ ግን ነገሮች የተቀየሩ እንደሚመስሉ አትተዋል።
በምርጫ 97 ወቅት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ኦሪሊያ ብራዚል ቀጣዩን ምርጫ እርሳቸው ከታዘቡት ጋር ማነጻጸርን መርጠዋል። በመረጃ ማግኘት በኩል ሰፊ ልዩነት እንዳለም ገልፀዋል። በሽግግሩ ወቅት አዲስ አበባ የነበሩት ማርክ ባስ የምርጫ ሂደቱ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል። ሂደቱንም ኢትዮጵያውያን ራሳቸው በባለቤትነት መምራት ይገባቸዋል የሚል ዕምነታቸውን አንፀባርቀዋል።




